ከኮቪድ-19 ወረርሺኝ በህብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን የጤና ችግር ለመቅረፍ አላማን አንግቦ የተጀመረው የድሬዳዋ ሁሉን አቀፍ የማህበረሰብ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በድሬዳዋ ምድር ባቡር አደባባይ በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደ የ2ኛው ሁሉን አቀፍ የማህበረሰብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትሜንት ቢ ኃላፊ አቶ ከዲር ጁሀር በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ከተለያዩ በሽታዎች ራሱን ለመጠበቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ በማዘውተር ተሳትፎውን ማጎልበት ይገባዋል ብለዋል፡፡ በማዘውተሪያ ስፍራዎች እና በትምህርት ቤቶች ላይ በመሰል እንቅስቃሴዎች መጠናከር እና በስፖርት ልማት ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የማህበረሰቡን የስፖርት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡
የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ በበኩለቸው ይህ ሁሉን አቀፍ የማህበረሰብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደ ድሬዳዋ በተለያዩ አካባቢዎች ቀደም ብሎ መጀመሩን እና ውጤት እየተመዘገበበት ያለ መሆኑን ገልጸው የማስ ስፖርት እንቅስቃሴዎች በዋነኛነት ጤናማ ህብረተሰብ ከመፍጠር ባለፈ የነዋሪውን የአብሮነት እሴት የሚያጠናክሩና አንድነትን ሰላምን እንዲሁም የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ በየጊዜው በእረፍት ቀናቶች ማለዳ ማለዳ ላይ ህብረተሰቡ በሚኖርበት አካባቢ ነዋሪዎች ለጤናቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በባለሙያ በታገዘ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ይህ የከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በየወሩ ለማካሄድ ኮሚሽኑ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተሳተፉ ነዋሪዎች እንደገለጹት በኮረና ወረርሺኝ ምክኒያት ከስፖርቱ በመራቅ ያሳለፈው የድሬዳዋ ነዋሪ መሰል የጤና መጠበቂያ ብሎም የስፖርት ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሳይቆራረጥ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴው በቀጣት አሁን ካለው በበለጠ መልኩ በባለሙያዎች በታገዘና የዕድሜ ካታጎሪን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቋል፡፡


