በድሬዳዋ የተለያዩ ቀበሌዎች በምሽት የሚከናወነው የአካባቢ ፀጥታ ጥበቃ ተግባር ሊበረታታ ይገባል ተባለ::

    ከተጀመረ ሳምንታትን ያስቆጠረውና መላው የድሬዳዋ ነዋሪ በራሱ ተነሳሽነት ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት እያከናወነ የሚገኘው የምሽት የአካባቢ ፀጥታ ጥበቃ (ሮንድ) ተግባር፣ የተሻለ ውጤት እየተገኘበት እንደሚገኝ ተገልጿል::
    ይህንን የአካባቢ ፀጥታ ጥበቃ ተግባር የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ ጣሀ እና የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጉሌድ ድርዬ፣ በሁሉም የከተማ ቀበሌዎች በምሽት ተዘዋውረው በመመልከት ተሳታፊዎቹን አበረታተዋል::
    በምልከታው ወቅት በሮንድ ስራ ላይ የነበሩት ነዋሪዎች በንግግራቸው፣ ድሬደዋን ወደ ቀድሞ ሰላሟ ለመመለስ፣ ከምንግዜውም በላይ በአካባቢያቸው ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ፣ ከፖሊስ ጋር በባለቤትነት ስሜት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል::
    አያይዘውም “አመራሮቹ በምሽት በየመንደሩ በአካል ተገኝተው ምልከታ ማድረጋቸው ለተሻለ አጋርነት ያነሳሳናል” ያሉ ሲሆን፣ የፀጥታ ስራውን የሚያግዙ ግብአቶች እንዲሟሉላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል::
    ከፍተኛ የፀጥታ ኅላፊዎቹ በበኩላቸው፣ መላው ህብረተሰብ ለአካባቢው ሰላም ይመለከተኛል በማለት፣ የምሽቱን ብርድ ተቋቁሞ እያከናወነ ለሚገኘው የአካባቢ ፀጥታ ጥበቃ ተግባር ምስጋና አቅርበው፣ በቀጣይ ቀናት ለዚህ መልካም ተግባር አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የማሟላትና የማደራጀት ስራ በፍጥነት እንደሚከናወን አረጋግጠዋል::
    መረጃው ከድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት የተገኘ ነው