በሀገራችን ትምህርትን ለዜጎች ከማድረስ አንፃር ባለፉት አመታት ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም ይሁን እንጂ አሁን ላይ በርካታ የሀገራችን ዜጎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ቢገኙም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ አይገኙም፡፡
ይህንንም ችግር ለመፍታት ይረዳ ዘንድ በትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ባለፉት አመታት ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ስራዎች መሰራት ተችሏል፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደርም በራሱ ተነሳሽነት በ 2010 ዓ.ም በ 06 ቀበሌ በሚገኘው ህዳሴ ትምህርት ቤት 120 ለሚሆኑ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በማካሄድ የጀመረው አቶ ወስን ቢራቱ አሁን ላይ በከተማዋ ላይ የሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች ላይ ለሚማሩና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ከ 700 በላይ ተማሪዎች ከሰኞ እስከ አርብ የምገባ ፕሮግራሙን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የምገባ ፕሮግራሙ በከተማዋ ላይ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ሲካሄድ ብሄር፣ ዘር፣ ሀይማኖት ሳይል ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም የምትታወቅበትን በጋራ አብሮ የመኖር እሴትን የሚያጎለብት አንድ አላማን በማንገብ በመካሄድ ላይ ከመሆኑም በዘለለ ፕሮግራሙም የተማሪዎችን አንድነትና መተሳሰብን በማጠናከር ነገ ላይ ለሀገሩ የሚጠቅም ትውልድን ለማፍራት በመንቀሳቅስ ላይ እንደሚገኝ አቶ ወስን ቢራቱ ተናግሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ተናግሯል፡፡
በምገባ ፕሮግራሙም ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ምግ ሳይመገቡ ወደ ትምህርት ቤት በሚመጡበት ወቅት ለተለያዩ የጤና ችግር ይጋለጡ እንደነበር ጠቅሰው ነገር ግን አሁን ላይ አቶ ወስን ቢራቱ እያደረገላቸው ያለው በጎ-ተግባር እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል ፡፡


