የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተ በኋላ በየቀኑ የሚያዙ የቫይረሱ ተጠቂዎች ብዛት በጣት የሚቆጠር ቢሆን አሁን ላይ በየቀኑ ከ400 እስከ 500 የሚሆኑ ዜጎች በቫይረሱ እየተያዙ ይገኛሉ ፡፡ የመያዝ ቁጥሩ አነስተኛ በሆነበት ወቅት ቁጥጥሩ ጠንካራ የመሆኑን ያህል ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቫይረሱ በየቀኑ እየተያዙ ጥንቃቄ የሚባለው ነገር ተዘንግቷል መዘናጋቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡
‹‹ እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ ›› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚጀመረው የንቅናቄ ስነ-ሰርአት በአስተዳደሩ የማስክ ማድረግ የንቅናቄ መርሀ ግብር ተጀምሯል፡፡
በንቅናቄ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ እንደተናገሩት በሀገራች ይህን አሳሳቢ ችግር በፍጥነት መቀየር ካልቻልን የሚደርሰው ጉዳት ከአቅም በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳይፈጠር በአስተዳደሩ የሚገኙ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ደንበኞችን ማስክ መልበሳቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል በማለት በአገልግሎት ሰጪዎች በተመሳሳይ መልኩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ የማድረግ ግዴታ አለባቸው ብለዋል፡፡
ከንቲባ አህመድ ከዚህም ጋር አያይዘው የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ በማይለብሱ አገልጋዮችም ሆነ ተገልጋዮች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ይህ ንቅናቄ በሂደት ወደ ተለመደ አሰራር እነዲሸጋገርና ለኮሮና መከላከል ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኝ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገለጸዋል ፡፡
ከቤት ውጭ በሚኖረን እንቅስቃሴ በተለይም በትራንስፐርት፣ በአገልግሎ ሰጪ ተቋማት ፣ በእምነት ተቋማት ፣በገበያ ስፍራዎች በአግባቡ የፊት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭብል በማያደርጉ የህግ አስከባሪዎች የንቅናቄ መርሀ ግብሩ የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበተክቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
‹‹ እንድናገለግሎ ማስክዎን ያድርጉ›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው መርሀ ግብር የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በህብረተሰቡ ዘንድ ለኮሮና ቫይረስ የተሰጠው ትኩረትና እየጨመረ የመጣው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍለን ማስክ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
‹‹ እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ ›› በሚል መሪ ቃ በተዘጋጀው የመርሀ ግብር ላይ የተሳተፉ የባለድርሻ አካላትም በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ከጤና ችግር ባሻገር እየተከሰቱ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም የሚያባብስ በመሆኑ የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ በተቋማቸው አገልጋዮችም ሆነ ተገልጋዮች እንዲለብሱ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡
በፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ተወካይ የሆኑት አቶ በላይነህ ከበደ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመቆጣጠር፣ ለመከላከልና ብሎም ለመግታት የወጡትን መመሪያዎች ህብረተሰቡም ይሁኑ አገልግሎት ሰጪ አካላት ሊያከብሯቸው እንደሚገባና መመሪያውን በማያከብሩ ላይ በመመሪያው ላይ የተቀመጠውን እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ እስራትና ሌሎች ቅጣቶችን ተፈፃሚ ከማድረግ አንፃር ህግ አስከባሪዎች እና ባድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የበሽታውን ስርጭት አስመልክቶ ያሉ ሃገርአቀፍና አስተዳደራዊ እውነታዎች የቀረቡ ሲሆን ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ በሽታ ተይዘው በተደረገላቸው የህክምና እርዳታ ያገገሙ ሁለት የከተማችን ነዋሪዎች የወረርሽኙን አስከፊነት ከተሞክሯቸው በመመስከር ህብረተሰቡ ቸልተኝቱን ወደ ጎን በማድረግ ማስክ ከማድረግ ጀምሮ ያሉ አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን እንዲወስድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡


