በድሬዳዋ የኢትዮጵያ ቴኒስ ሻምፕዮን ውድድር በዛሬው እለት ተጀመረ።

    የድሬደዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሸን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ ውድድሩን በይፋ ሲከፍቱ እንደተናገሩት የኢትዮያን መሰብሰቢያ የሰላም ፣ የፍቅርና የአብሮነት ከተማ ድሬደዋ ይህ ጨዋታ እንዲህ በደመቀ መልኩ ለማካሄድ ዕድል በማግኘታችን በራሴና በኮሚሽኑ ስም ያለንን አድናቆት መግለጽ እወዳለሁ ብለዋል።
    ኮቪድ 19 በስፖርቱ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ተቋቁሞ የቫይረሱን ስርጭት እየተከላከሉ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን ጠብቀው ሀገር አቀፍ ውድድር ከጀመሩት አንዱ የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን በመሆኑ ይህንን ውድድር የስፖርተኞችን ስፖርታዊ ብቃት የሚመዘንበትና ክህሎታቸውን ለማሳደግ ልምድ የሚቀሰምበት ከመሆኑም ባሻገር የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር ወንድማማችነትን ፣ አብሮነትና ፍቅርን ያሳድጋል ብለዋል፡፡
    የኢትይጵያ ቴኒስ ስፖርት የክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ሻምፒዮና እንዲሁም የጤና ቡድኖች ውድድር በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ክልሎች ልዑካን ቡድን አባላትና ለኢትዮዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ተሳትፎ ላደረጉ የልዩ ልዩ ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው ውድድሩን በይፋ ከፍተዋል።
    የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት በቀለ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት የቴኒስ ስፖርት በአገራችን ተወዳጅ እና ተዘውታሪ እንዲሆን እየሰራን ነው ብለዋል።
    በዚህ ውድድር ምርጥ ተተኪ ስፖርተኞችን በመመልመል በክልሎች እንዲሁም በአገራችን በአህጉር እና በአለም አቀፍ ውድድሮች አገራችንን በመወከል መልካም ስም በስፖርቱ ለመገንባት የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።
    በስፖርታዊ ጨዋነት ለሚሳተፉና የተሻለ ክህሎት ላሳዩ ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳደር ተወካዮች ለሻምፒዮና ስፖርተኞች ፌዴሬሽኑ የማበረታቻ ሽልማት ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
    ይህ ውድድር እንዲሳካ ከፋተኛ እገዛ ላደረጉ ለድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ለድሬዳዋ ቴኒስ ፌዴሬሽን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
    በውድድሩ ለመሳተፍ ለመጡ ስፖርተኞችና አሰልጣኞች በመልካም ፉክክር እንዲጠናቀቅ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።