በድሬዳዋ በዘጠኙም ቀበሌዎች የፅዳት የንቅናቄ ዘመቻ በዛሬው እለት ተጀመረ፡፡

    በአሰተዳደሩ ዘጠኙም ቀበሌዎች መንደሮችን በመስፈርት በመምረጥ ሞዴል መንደሮችን ለመፍጠር እንዲሁም በተመሳሳይ ለንቅናቄና ለዘመቻ ፅዳት በመስፈርት ለይቶ በመምረጥ የፅዳት ስራዎችን ለማከናወን ከተማ አቀፍ የፅዳት ህዝብ ንቅናቄ (ሲፀዳ መንደሬ ትዋባለች ድሬ)የሚለውን መሪ ቃል በመያዝ በአስተዳደሩ እስከ ሰኔ ሰላሳ ድረስ በየሳምንቱ የሚቀጥል ዘመቻ በዛሬው እለት ተጀምሯል።
    የከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ በዘመቻ ስራው ላይ እንደተናገሩት ዘመቻው በቀጣይ ጊዜም በሳምንት አራት ቀበሌዋችን በመምረጥ እንደሚካሄድ በመግለፅ ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ቁሻሻን የሚጠየፍ ማህበረሰብ እንዲኖር ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
    ኃላፊው ከዚህም ጋር አያይዘው ቀደም ሲል የነበረው የፁዳት ዘመቻዎች ህዝባዊ መሰረት ባለመኖሩ በተፈለገው መሠረት መስራት አለመቻሉን ጠቁመው ከተማዋን ፁዱ ለማድረግ ከመንደራችን ጀምረን በማፀዳት ኃላፊነታችንን ለመወጣት ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
    በከተማዋ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ መንግስት ብቻውን ከተማዋን ማፁዳት ባለመቻሉ እያንዳንዱ ነዋሪ አካባቢውን በ 20 ሚትር ርቀት ድረስ በማፁዳት የከተማዋን ውበት መጠበቅ አለባቸው ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
    የአስተዳደሩ ፅዳትና ውበት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጣሂር ሮብሌ በበኩላቸው እንደተናገሩት በቀጣይ የዘመቻውን ስራ በማጠናከር በተረፈ ምርቱን ወደ ኮሙፖስትነት በመቀየር ለወጣቱ የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
    የፀዳት ዘመቻው በነገው እለትም በቀበሌ 09 እና 06 እንደሚካሄድ የኤጀንሲው ኃላፊ አስታውቀዋል።
    በፀዳት ዘመቻው የተሳተፉ ነዋሪዋች በሰጡት አስተያየት አካባቢያቸውን በማፁዳት ድሬዳዋ ቀድሞ የነበራትን ስሟን ለመመለስ የበኩላቸውን ለመውጣት በአካባቢያቸው የሚኖሩ ወጣቶችን በማስተባበር በዘመቻው መሳተፉቸውን ገልፀዋል።