በ 01ቀበሌና በገንደ ሪጌ ገጠር ቀበሌ በፓየኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ በድሬዳዋ አስተዳደር ህብረተሰብ ተሳትፎ እና ልማት ኤጀንሲ እንዲሁም በፌደራሉ የማእድንና ነዳጅ ሚንስትር የጋራ ትብብር የተከናወኑና ለመከናወን በእቅድ የተያዙ የልማት ስራዎች ምርቃና ጉብኝት ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ ላይ የማእድንና ነዳጅ ሚንስትር ሚንስቴር ዲኤታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ ሚንስትር መስሪያቤቱ ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ የሚኖረውን ሚና በማሳደግ ተልዕኮውን ለመወጣት በሚያስችለው መልኩ በአዲስ የለውጥ መንፈስ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።መንግስት በዚህ የለውጥ ወቅት በየደረጃው ያለውን ማህበረሰብ ክፍል በየአካባቢው ከሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ እየቀየሰና ያለውን ውስን ሀብት እያቀናጀ የልማት አጋሮቻችን እያስተባበረ ህዝቡ በተጨባጭ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ በየአካባቢው ከሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ ከሚሆንባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የልማት ፕሮጀክት ባለፈቃዶች የማህበረሰብ ልማት ፈንድ እንዲገቡ በማድረግ በነዋሪው ጥያቄ መሰረት የአካባቢውን ተጨባጭ ችግሮች የሚቀርፉ ልማቶችን ማከናወን ነው ተብለዋል።በዚህ መሰረት በድሬደዋ በፓየኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ የተገነባው 700 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 250 ኪሎ ዋት የሚሸከም የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ግንባታ የዚህ ማሳያ መሆኑን ሚንስቴር ደኤታዋ ገልፀዋል ።
በሌላ በኩል የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በአስተዳደሩ ከድርጅቶቹ ከፋብሪካዎች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ሀብት በማፈላለግ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በድሬደዋ የኖራ ድንጋይ / ላይም ስቶን / ምርት ፈቃድ ወስደው እሰሩ የሚገኙ ኩባንያዎች የማህበራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ከማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ጋር ውል ከገቡት የፖየኔር ሲምቶ ፋብሪካ ከተሰበሰበ ከዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ሺ ብር በላይ እንዲሁም ከመንግስት በተደረገ ከስምንት መቶ ሀምሳ ዘጠኝ ብር በላይ በጥቅሉ ከአንድ ሚሊየን ስምንት መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ የኤሌክትሪክ ሀይል መስመር ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል።በቀጣይም በገንደ ሪጌ ገጠር ቀበሌ የውሃ መስመር ስርጋታ ለማከናወን እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
መንግስት ሁሉንም የልማት ጥያቄዎች በብቸኝነት የመፍታት የአቅም ውስንነት እንደመኖሩ መጠን ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን በመወጣት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ከግብ እንዲደርስ መደገፍ እንዳለባቸው አቶ ከድር ጁሃር ጥሪ አቅርበዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ህብረተሰብ ተሳትፎና ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ጎንፋ አራርሳ በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ ቀበሌዎች የመንገድ መብራት ዝርጋታ የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ የውሀ መስመር ዝርጋታን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲሁም በመንግስት ድጋፍ መከናወናቸውን ጠቁመዋል።


