የኢትዮጰያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዪት የ2 ኛው የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።

    ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የኢትዮጲያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ 2013 በጀት ዓመት 2ኛው የህብረተሰብ ጤና ፎረም በዛሬው እለት በድሬዳዋ ተጀምሯል፡፡
    የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በመክፈቻ ንግግሯ እንደተናገረችው ድሬዳዋ ዙሪያዋን 38 ገጠር ቀበሌዋች የሚገኙባት ከተማ በመሆኖ የተለያዩ የጤናና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ያለንን ውስን የሰው ኃይል ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጲያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የጤና ሚኒስተር በገንዘብ፣ በባለሞያና በስልጠና እንዲሁም በተለያዩ ነገሮች ከጎናችን ሳይለይ ሰፊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ተናግረው ለተደረጉ ድጋፎችና ሞያዊ እገዛዎች በአስተዳደሩና በነዋሪው ህብረተሰብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
    ወ/ሮ ለምለም አክለውም ለአስተዳደሩ የሚደረገው ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን በመጠቆም የፎረሙ ተሳታፊዎች በቀጣይ ቀናት የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
    የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጲያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ጥበቃ ሚ/ር እና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን በሀገራችን የሚከሰቱ የተለያዩ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከልና ሲከሰቱም ችግሩ ሳይስፋፋ የመቆጣጠርና ምላሽ የመስጠት እንዲሁም በችግሩ የተጎዱትን መልሶ የማቋቋም ሥራ ይሰራል ያሉ ሲሆን የድሬደዋ ከተማም በተለያዩ ምክኒያቶች በተለላላፊ በሽታዎች በተለይ የደንጊ ትኩሳት፣ ችኩንጉኒያና የጎርፍ አደጋ ሲከሰት ድጋፎች ሲደረጉ እንደነበር አስታውቀዋል።
    የፎረሙም ዓላማ ፌደራልና ክልሎች ብቻ ሳይሆን ክልሎች እርስ በእርስ መተጋገዝ እንዲችሉ በማድረግ ወንድማማችነት የሚጠናከርብትን መንገድ ማመቻቸትና ለማህበረሰቡ ቀድሞ በመድረስ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተጋግዞ ምላሽ መስጠት እንዲቻልና አንዱ ከሌላው ያለውን ጠንካራ ጎን በመውሰድ ለማስፋፋት መሆኑን ተናግረው መድረኩን ላመቻቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
    ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በመድረኩ ሪፖርቶች፣ ፅሁፎችና የተሳታፊዎች ውይይት እንደሚኖር ከአስተባባሪዎቹ የተገኛው መረጃ ያመላክታል፡፡