አሽከርካሪዎች በትራፈክ ደንብ መተላለፍ ሲቀጡ በዘመናዊ የባንክ ክፍያ ስርአት ታግዘው ክፍያቸውን ባቅራቢያቸው በሚያገኙት የአቢሲኒያ ባንክ እንዲፈፅሙ ለማስቻል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታወቀ።

    በአተገባበሩ ላይ ለትራፊክ አባላትና ለትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰቷል፡፡
    በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንደመልካም አስተዳደር ችግር ሲነሱ ከነበሩ ችግሮች አንዱ የዘመነ የቅጣት ክፍያ ስርአት ባለመኖሩ የሚደርሱ ተገልጋይ እንግልቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
    ይህንኑ ችግር በዘላቂነት እንደሚቀርፍ የታመነበት ዘመናዊ የክፍያ ስርአትን ለመተግበር ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር ስምምነት በማድረግ አሽከርካሪዎች የቅጣት ክፍያቸውን በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች መክፈል እንዲችሉ ለማስቻል ዝግጅት መደረጉን ነው የተጠቆመው፡፡
    ይህንኑ ስርአት ለትራፊክ አባላት፤ለትራንስፖርት ተቆታጣሪዎችና ለእለት ገንዘብ ሰብሳቢዎች ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰአዳ አዋሌ እንደተናገሩት ተቋሙ የደንበኞች እርካታ ላይ በስፋት እየሰራ እንዳለ ጠቁመው በተለይ በደንበኞች ከሚነሱ ቅሬታዎች መካከል ከቅጣት ከፍያ ስርአት ጋር ተያይዞ ያለውን ለመፍታት በተሰራው ስራ አሁን ላይ ክፍያውን በባንክ ስርአት በዘመነ መልኩ ደንበኞች ካሉበት ሆነው እንዲፈፅሙ ለማስቻል ስምምነት በማድረግ ወደትግበራ ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡
    በቀጣይም ሁሉንም የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ደንበኞች በአገልግሎታችን እንዲረኩ እንሰራለን ለዚህም የተገልጋይ ገንቢ አስተያየቶችና ጥቆማዎች ያስፈልጉነል ነው ያሉት፡፡
    በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጉልማ ታዬ በበኩላቸው ይህ የክፍያ ስርአት ተግባራዊ መሆን ተገልጋዩ በመስኮት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአት ላይ ያነሳው የነበረውን የአገልግሎት አሰታጥ ክፍተት ከመሙላቱም በዘለለ የተቋሙን የአገልግሎት አሰታጥ ስርአት ወደዘመናዊ የአሰራር ስርአት ለማሳደግ በሚደረገው ጉዞ አንድ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
    ይህም በተለይም በትራፊክ ደንብ መተላለፍ ሚቀጡ አሽከርካሪዎች በእንግልቱ ጊዜና ጉልበታቸውን አእንዳያባክኑም ሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
    በእለቱ ስልጠናም የትራፊክ ፖሊሶችም ሆኑ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች እንደሁም የእለት ገንዘብ ሰብሰቢዎች የአሰራር ስርአቱን በሚገባ ተረድተው ወደስራ እንዲገቡ ታስቦ መዘጋጀቱንና ስልጠናውም በሁለት ዙር መሰጠቱን ነው የተናገሩት።