የ125ኛው የአድዋ ድል በዓል“ዓድዋ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት አርማ!”

    በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ አስተዳደር ሲከበር የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ያደረጉት ንግግር፡-
    አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ጅረት ውበቷ ያልደበዘዘ፣ዛሬም እንደ ጥንቱ አምራና ተውባ ያለች ድንቅ አገር ነች፡፡ ምድረ-ቀደምት የሆነችው አገራችን የፍቅርን ማዕድ አብረው የሚቋደሱ፣ሰላምና አንድነት ሸማቸው የሆኑ ህዝቦች ባለቤት ነች፡፡
    ይህችን የዓለም ህዝብ ቀልብ የሳበች ምድረ-ገነት አገርን ደግሞ ያወረሱን የአድዋ ከዋክብት የሆኑት ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ናቸው፡፡
    በኢትዮጵያውያን አቡሻኽር (Julian calendar) የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ወይም በአውሮጳውያን የዘመን አቆጣጠር (Gregorian Calendar) February (የካቲት) መጨረሻ እና March (መጋቢት) መጀመሪያ ላይ 1896 ለጦርነቱ መነሻ የሆነው ውል የተፈፀመው በዚሁ ዘመን ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ ከውጫሌ ከተማ ግርጌ ከአምባሰል ተራራ ሥር ወሎ ውስጥ ንጉሥ ይስማ እየተባለ በሚጠራ ሥፍራ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
    ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮጳ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጠናል ሲል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ “የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ” በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፉ ላይ ከትቧል፡፡
    ይህ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በባዶ እግር ሆነው ዘመነኛውን የጣሊያን ጦር ድባቅ የመቱበት የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን የነፃነት ብርሀንን የፈነጠቀ ነው፡፡ እብሪተኞች ያፈሩበት፣የተናቁት የከበሩበት፣ የአልችልም ባይነት ቀንበር የተገፈፈበት ነው፡፡ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡
    አድዋ የደምና የአጥንት መስዋዕትነት ዋጋ ነው፡፡ ትላንት አገራችንን ደማቸውን አፍስሰው፣አጥንታቸውን ከስክሰው ይህችን የዓለም ህዝብ በጉጉት የሚያያትን አገር የአድዋዎቹ ጀግኖች አርበኞቻችን አስረክበውናል፡፡ የዛሬው መስዋዕትነት በቅንነትና በትጋት አገራችንን ማገልገል ነው፡፡ ጥንተ ጠላታችን ድኅነትን በተባበረ ክንድ ድል መንሳት ነው፡፡
    ብዝሃነትን ለአድዋ ድል በመጠቀም አርአያችን የሆኑትን የአድዋ አርበኞቹን ፈለግ በመከተል ብዛሃነታችንን ለአገር አንድነት፣ለአገር ዕድገት ለማዋል መስራት ይጠበቅብናል፡፡
    አድዋ “የህብረ ብሔራዊ አንድነት አርማ” በሚል መሪ ቃል 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል ስናከብር ጀግኖች አርበኞች ለዋሉልን ውለታ ምስጋናና አክብሮት ከመቸር ባለፈ በብዙ ድካምና ዋጋ ያቆዩልንን አገራችንን ህብረብሄራዊ ማንነታችንን በመጠበቅና የብልፅግና መንገዳችንን ከግብ በማድረስ የድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡
    አድዋ ወጣቶች ታሪካቸውንና ማንነታቸውን እንዲያውቁ መሠረት የጣለ ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቶች ከአድዋ ድል የተገኙትን የአገራዊ ፍቅርን፣የአንድነትንና የጀብደኝነትን ትሩፋቶች በግብር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
    ወጣቶች በአድዋ ድል ብቻ ሳይኩራሩና ሳይቆዝሙ የራሳቸውን ዘመን ደማቅ ታሪክ መፃፍ፣የራሳቸውን ዘመን አዲስ ገድል ማኖር አለባቸው፡፡
    በመጨረሻም ይህን የአገር ኩራት፣የዘመናት ንግስናን ያጎናፀፈንን የአድዋ ድል በዓል ሥነስርዓት ባማረ ሁኔታ ላዘጋጁልንና ላስተባበሩልን የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤትና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
    አመሰግናለሁ!