ከመብራት አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የከተማዋ ነዋሪዎች ሲያነሷቸው የነበሩትን ጥያቄዎች ከመፍታት አኳያ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራታቸው ተገለፀ ።

    በከተማችን ድሬዳዋ ከመብራት አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ነዋሪዎች ሲያነሷቸው የነበሩትን የተለያዩ ጥያቄዎችን ከመፍታት አኳያ የድሬዳዋ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰራቸውን ስራዎች አስመልክቶ የተቋሙ ሀላፊ የሆኑት አቶ ፍቅረማርያም አለማየሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ። በተለይም ከአስቸኳይ ጥገና ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የነበረውን አሰራር በመቀየር በዘመናዊ መንገድ አገልግሎቱን በመስጥትና በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የደንበኞችን ቅሬታ ከመፈታቱም በዘለለ ከዚህ ቀደም በሰውና በንብረት ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮችንም መፈታት መቻሉን በኢትዮጲያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈፃሚና የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍቅረማርያም አለማየሁ ገልፀው ደንበኞች የአስቸኳይ ጥገና አገልግሎት ፈልገው ወደ ተቋሙ በሚደውሉበት ወቅት አፋጣኝ የሆነ ምላሽ እንደተደረገና የጥገና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትም ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራታቸውንም ነው አቶ ፍቅረማርያም የተናገሩት።
    ሀላፊው አክለውም ከዲጂታል ክፍያ ጋር ተያይዞ ቴክኖሎጂን ባማከለ መልኩ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን ፍላጎት ማሟላት ከመቻሉም ባለፈ በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የመብራት አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩና ለአብነትም በአንድ መንደር የሚገኙ ከ 1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዎሪዎች የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አቶ ፍቅረማርያም ገልፀዋል ።
    አሁን ላይ ተቋሙ እየሰራቸው ያሉትን ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና የከተማው ነዋሪዎችም ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉት ስራዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ የተለመደ ትብብራቸውን ማድረግ እንደሚገባቸው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈፃሚና የድሬዳዋ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍቅረማርያም አለማየሁ ተናግረዋል ።