በድሬዳዋ አስተዳደር በ 2013 በጀት አመት ባለፍት 6 ወራት 157 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ ።በቀጣይም ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ነዋሪው ህብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ተገልፃል ።

    በጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ በዋናነት ገቢን በመሰብሰብ ፣ ኮንትሮባንድን በመከላከልና የተለያዩ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ ሀገራችን ኢትዮጲያ የውጪ ምንዛሬን እንድታገኝ ከማድረግ አኳያ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ። በዚህም መሰረት በ 2012 በጀት አመት ከ 6 . 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 8 . 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ። ኮንትሮባንድን ከመከላከል አኳያም 108 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ታቅዶ 234 . 25 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን በጉምሩክ ኮሚሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ደመላሽ ተሾመ ተናግረው የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደተለያዩ ሀገራት በመላክም 150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ከ 149 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን አቶ ደመላሽ ተሾመ ተናግረዋል ።
    አቶ ደመላሽ አክለውም በ 2013 በጀት አመት ባለፍት 6 ወራት ገቢን ከመሰብሰብ አኳያ 4 . 32 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 3 . 5 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል ። ኮንትሮባንድን ከመከላከል አኳያም ባለፍት 6 ወራት 95 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ታቅዶ 157 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ ደመላሽ ተናግረው 72 ሚሊዬን ብር የሚገመት የአሜሪካን ዶላር ወደ ውጪ ሀገራት ከሚላኩ ምርቶች ለማግኘት ታቅዶ 67 . 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሰብሰብ እንደተቻለና ህብረተሰቡም የኮንትሮባንድን አስከፊነትና ጎጂነት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበትና የጉምሩክ ኮሚሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋር በመሆን የኮንትሮባንድ አስከፊነትን ለህብረተሰቡ ማስተማሩ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ነው በጉምሩክ ኮሚሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ደመላሽ ተሾመ የገለፁት ።