ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አገጣጠምና ጠቀሜታው ላይ ያተኮረ ስልጠናን ለህዝብ እና ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችና ባለንብረቶችእንደሁም ለትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችና የትራፊክ አባላት ሰቷል፡፡
በያዝነው ወር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ በርካቶች ለህልፈት እንደሁም ለአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ሰለባ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡
ለነዚህ አደጋዎች በመንስኤነት ከተለዩት መካከል አንዱና ዋነኛው ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር መሆኑን የገለፁት በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰአዳ አዋሌ ናቸው፡፡
በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ለህዝብ እና ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች፤ማህበራት እንዲሁም የትራፊክ አባላትና ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች በፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አገጣጠምና ጠቀሜታው ላይ ባተኮረው ስልጠና ላይ እንደተናገሩት አሁን ላይ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሚሞቱ ወገኖቻችንን ህይወት መታደግ ካለብን እንደተቋም ተግባራዊ ምላሽ ያሻል ለዚህም የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያን ወደ ትግበራ ለማስገባት ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል፡፡
ፍጥነት ገዳይ ነው ለዚህም ማሳያ ከሰሞኑ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እየደረሱ ያሉ አደጋዎች ናቸው ያሉት ወ/ሮ ሰአዳ እንደ አስተዳደር የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ከምናደርገው የማስተማርና ማስግዘብ ስራ በተጓዳኝ መሰል ህጎች እንዲከበሩ ተሽከርካሪዎቻችንም ፍጥነታቸውን ጠብቀው እንዲያሽከረክሩ የቁጥጥር ስርአቱን በማጠናከርና እንደተቋም ከሚያዚያ አንድ ጀምሮ ማንኛውም ተሽከርካሪ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያን እንዲያስር ህጉን በማስከበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ይሰራልም ብለዋል፡፡
ለትግበራው ውጤታማነት የእለቱ ሰልጣኞች አሽከርካሪውላይ ግንዛቤ በመፍጠርና ለህጉ ተፈፃሚነት በመስራት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ወ/ሮ ሰአዳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ኮማንደር ጉሉማ ታዬ በበኩላቸው የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያውን በቅድሚያ ህዝብን በሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችና በጭነት ተሽከርከሪዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ የጠቆሙ ሲሆን በዚህም የምርት ዘመናቸው እንደ ኤሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2ሺ አመተ ምህረት ጀምሮ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ሁሉ መሳሪያውን የመግጠም ግዴታ እንዳለባቸው በመረዳት ለትግበራው እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የእለቱ ስልጠናም በፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ጠቀሜታና አተገባበሩ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


