በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ ስርጭት ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች የህክምና አገልግሎት መስጠት አዳጋች እየሆነ መምጣቱ ተገለፀ ።

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በአለም አቀፍም ሆነ በሀገራችን እንዲሁም በአስተዳደራችን ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች በሀገራችንም ሆነ በአስተዳደራችን ሲሰሩ ቢቆይም ከጊዜ ወደ ጊዜ በበሽታው የሚያዙ ፣ በፅኑ የሚታመሙና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመሩ መጥቷል ።
    በከተማችን ድሬዳዋ ላይም እስካሁን ድረስ 30.537 ናሙና ተመርምሮ 3.196 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የ 33 ሰዎች ህይወት ደግሞ ማለፍን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረው በ 1 ሳምንት ውስጥ ብቻ ከተመረመሩት 380 ሰዎች ውስጥ 125 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የ 3 ሰዎች ህይወት ማለፍን ወ\ሮ ለምለም ተናግረዋል ።
    ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማችን ድሬዳዋ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በበሽታው ተይዘው በፅኑ ለሚታመሙ ሰዎች የሚሆን የኦክሲጅን እጥረት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ወ\ሮ ለምለም ተናግረው ነገር ግን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አቅሙ በፈቀደ መልኩ ስርጭቱን ለመግታት እንዲሁም በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ለማከም ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።
    የከተማው ነዋሪዎች ከምን-ጊዜውም በላይ የበሽታውን አስከፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአፍና አፍንጫ ማስክ በመልበስና አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቅ እንዲሁም እጆቻቸውን በየጊዜው በማፅዳት የኮሮና በሽታን መከላከል እንደሚገባም የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ወ\ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ።