በድሬዳዋ አስተዳደር የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለፀ ።

    የወባ በሽታ በትንኝ አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ሲሆን በተለይም ንፅህናው ባልተጠበቀና ባቆሩ ዉሀማ አካባቢ በሽታውን አስተላላፊ ለሆነው ትንኝ መራባት አመቺ ነው። የአስተዳደሩ ጤና ቢሮም የወባ በሽታን ለመከላከል ይቻል ዘንድ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም ከሀምሌ እስከ የካቲት 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 987 ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል ።
    በድሬዳዋ አስተዳደር የወባ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ ተናግረው ይህንንም የወባ በሽታ ለመከላከል ይቻል ዘንድ ከግሎባል ፈንድ በድጋፍ የተገኘው 287 ሺህ 732 የሚሆን አጎበር በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር ለሚገኙ ነዋሪዎች ከዛሬ ጀምሮ አጎበሩ እንደሚከፋፈልም አቶ ዩሱፍ ሰኢድ ተናግረዋል።
    አቶ ዩሱፍ ሰኢድ አክለውም ነዋሪው ህብረተሰብ አጎበርን የመጠቀም ልምዱ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ለህብረተሰቡ ስለ ወባ በሽታ አስከፊነት እንዲሁም የአጎበርን አጠቃቀም በተመለከተ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደሚሰራ ተናግረው በተለይም የወባ በሽታን ለመከላከል የህብረተሰብ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኙ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች አካቢያቸውን ከማፅዳት አንስቶ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም የወባ በሽታ ስርጭትን መከላከል እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ ተናግረዋል ።