በድሬዳዋ አስተዳደር በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት 21 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በህብረተሰቡ ተሳትፎ ኦጀንሲ ኃላፊነትና በዘጠኙም የከተማ ቀበሌዎች ቅንጅት በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ የልማት ስራዎች በውጤት ለማጠናቀቅም መንግስት ከሚመድበው በጀት በዘለለ ከህብረሰተቡ በገንዘብ፣ በጉልበትና በዓይነት ድጋፍ እንዲደረግ ይጠበቃል፡፡ ይህንን መሰረት ባደረገ መልኩ በቀበሌ 05 አስተዳደር በህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ሲቀርብ የነበረው ቀርሳ ተራ የገበያ ማዕከል አካባቢ የተገነባው ባለ ስምንት መቀመጫ መጸዳጃ ቤትና አስር ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችለው የሻወር ፕሮጀክት ግንባታው ተጠናቆ የምርቃት ስነ-ስርዓቱ ተከናውኗል፡፡
የአስተዳደሩ የህብረተሰብ ተሳትፎ ኤጀንሲ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጎንፋ ሞሲሳ እንዳሉት በአስተዳደሩ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን በተሻለ ጥራትና ተደራሽነት ለማከናወን በዝግጅት ምዕራፍ በዘጠኙም የከተማ ቀበሌዎች የሚገኙ የህበረተሰብ ተሳትፎ የኮሚቴ አደረጃጀቶችን በአዲስ መልክ በማደራጀት የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ወደስራ መገባቱንና አሁን ላይም ጠንካራ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ለማበረታታትና ህረተሰቡንም ለማገዝ በዚህ ዓመት ያለውን የኮረና ቫይረስ/ የኮቪድ 19 ጫና ታሳቢ በማድረግ ከመንግስት ይጠበቀ የነበረውን ተሳትፎ ወደ 70% (ሰባ በመቶ) ከፍ መደረጉን እንዲሁም ከህብረተሰቡ የሚጠበቀውን የተሳትፎ መጠንም ወደ 30% (ሰላሳ በመቶ) ዝቅ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በህረተሰብ ተሳትፎ ኤጀንሲ አስተባበሪነት ከመጸዳጃና ሻወር ቤት በዘለለም የህብረተሰቡን ጥያቄ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የቦኖ ውኃ ግንባታ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ዝርጋታና ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ቀደም ብሎ ሲሰሩ የነበረና በቀጠይም የሚሰራ ስለመሆኑ የኤጀንሲው ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡ በቀበሌ 05 አስተዳደር የተሰራው የመጸዳጃ ቤትና የሻወር ቤት ፕሮጀክት በመንግስት 55 % (ሃምሳ አምስት በመቶ) ወጪ በተደረገ በጀት እንዲሁም በህበረተሰቡ 45 % (አርባ አምስት በመቶ) አስተዋጽኦ መገንባቱን አቶ ጎንፋ ተናግረዋል፡፡ ይህ የልማት ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶች በተለየ መልኩ ከመንግስትና ከህብረተሰቡ ተሳትፎ በዘለለም ኤስ.ኦ.ኤስ (SOS) የህጻናት መንደር የተባለው ግብረሰናይ ድርጅትም የተሳተፈበት ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ከፕሮጀክቱም ጋር ተያይዞ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ህበርተሰቡ በአግባቡ ሊጠብቀው ይገባልም በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ኤስ.ኦ.ኤስ (SOS) የህጻናት መንደር በቀበሌ 05 አስተዳደር ድጋፍ ለሚያደርግላቸው ወላጀቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህጻናት ዘላቂ ገቢ ማግኘት እንዲችሉ ታሳቢ በማድረግ ለፍልውኃ አንድነት መረዳጃ እድር ባደረገው እገዛ አማካኝነት አጠቃላይ ለፕሮጀክቱ ከወጣው ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ 45% ( አርባ አምስት በመቶ) የሚሆነው የህብረተሰብ አስተዋጽው በመረዳጃ ዕድሩ የተሸፈነ ስለመሆኑ የነገሩን ደግሞ የፍልውኃ አንድነት መረዳጃ ዕድር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ እሸቱ ተንኮሉ ናቸው፡፡
መጸዳጃ ቤቱ መሰራቱ በቀርሳ ተራ ገበያ ነጋዴዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረውን የጋራ መጸዳጃ ቤት ጥያቄ መልስ ከመስጠቱም በተጨማሪ ከመጸዳጃና ሻወር ቤቱ አገልግሎት የሚሰበሰበው ገቢ ዕድሩ ለሚረዳጃቸው ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ህጻናት ድጋፍ እንደሚውል ሊቀመንበሩ ገልጸውልናል፡፡ ከማህበረሰብ አቀፍና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት በቅንጅት ጋር እንደዚህ ዓይነት ስራዎች ሲሰራ የመጀመሪያ ስለመሆኑና ስራዎቹ ለሌሎች አካላትም ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙ ሲሆን በቀጣይም ይህን መሰል የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የፕሮጀክት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል በማለት አቶ እሸቱ ተናግረዋል፡፡
በሀረር የኤስ.ኦ.ኤስ (SOS) የህጻናት መንደር የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አንዱአለም ጌታቸው እንዳሉት ኤስ.ኦ.ኤስ (SOS) የህጻናት መንደር እ.ኤ.አ ከ2016 በቀበሌ 05 አስተዳደር የቤተሰብና ማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ በማድረግ ከ1200 በላይ ህጻናትን በመደገፍ ስራውን የጀመረ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን የፕሮጀክቱ ራዕይ አንዱ ከማህበረሰቡ ጋር በጥምረት ህበረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረገ የልማት ስራ ላይ መሳተፍ በመሆኑ ይህንን የጋራ መጸዳጃ ቤትና ሻወር ፕሮጀክት እንዲሰራ እገዛ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ላይ በተወሰነ መልኩ መጓተቶች ቢኖሩም በዚህ ዓይነት መልኩ መጠናቀቁ በእርዳታ የሚገኘውን ሀብት ከህብረተሰቡ ከሚገኘው ጋር አቃናጅቶ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚቻል ያመላከተ ፕሮጀክት መሆኑ ገልጸዋል፡፡ ለግበረሰናይ ድርጅቱ ስራዎች ስኬት የቀበሌው ማህበረሰብ ፣ የቀበሌ 05 አስተዳደር ጽ/ቤት ፣ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ እንዲሁም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ላደረጉላቸው አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚና የቀበሌው ነዋሪ የሆነው ወጣት ሳሙኤል ፍስሀ እንዳለውም አካባቢው ላይ የሻወርም ሆነ የመጸዳጃ ቤት ባለመኖሩ ተቸግረው የነበረ መሆኑን ገልጾ አሁን ላይ ይህ ፕሮጀክት መሰራቱ የረጅም ጊዜ ችግራቸውን የሚቀርፍላቸው ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡ በፕሮጀክቱ ስራ ላይ ህበረተሰቡ በእኔነት ስሜት ሲሳተፍ የነበረ መሆኑን ጠቁሞ በቀጣይ መጸዳጃና ሻወር ቤቱ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደራሱ አድርጎ ሊጠብቅ ይገባል ብሏል፡፡


