ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታ በድሬዳዋ አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል ፡፡
በሽታው በሀገራችን ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በድሬዳዋ አስተዳደር 32 ሺህ 209 ለሚሆኑ ሰዎች የናሙና ምርመራ በማድረግ 3 ሺህ 718 የሚሆኑ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን እስካሁን ድረስም ከበሽታው ጋር ተያይዞ በከተማዋ የ 45 ሰዎች ህይወትም አልፏል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ መመሪያ ወቷል፡፡
ይህንን መመሪያ በድሬዳዋ አስተዳደር ተግባራዊ በሚሆንባቸው እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎች እራሳቸውን ከበሽታው መከላከልና መቆጣጠር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ፣ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም አቃቤ ህግ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የከተማው ነዋሪዎች በኮሮና ቫይረስ የመያዝ እድላቸው እየጨመረ ከመምጣቱም ባለፈ በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረው የከተማው ነዋሪዎችም የኮሮና ቫይረስ የመከላከያ መንገዶች የሆኑትን እጅ መታጠብ ፣ ርቀት መጠበቅና ማስክ ማድረግን መተግበር እንዳለባቸው ነው ወ/ሮ ለምለም የተናገሩት ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን መመሪያ ለማስተግበር የጋራ ትብብርን ስለሚጠይቅ ይህንንም ለማስፈፀም ይቻል ዘንድ ከድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ፣ ጤና ቢሮ ፣ ንግድና ኢንደስትሪ እንዲሁም የተለያዩ ግብረ ሀይሎች ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፈይሳ ሹርኬ ተናግረዋ።
በህጉ አግባብ የተቀመጡ የህግ ቅጣቶች መመሪያውን ተግባራዊ ባላደረጉ አካላት ላይ ተግባራዊ ሊሆን ስለሚችል ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የከተማው ነዋሪዎች ከበሽታው እራሳቸውን ከመከላከል ጎን-ለጎን በጋራ በመሆንና በመተባበር በሽታውን መከላከል እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረዋል፡፡


