በድሬዳዋ አስተዳደር በርካታ የግል፣ የማብረሰብ/የህዝብ እንዲሁም የእምነት ተቋማት ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በመሳተፍ መንግስት ትምህርትን ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽዎ በማበርከት የተማረ ዜጋ በማፍራት ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች በሚሰጡት የትምህርት አገልግሎትም ከየተማሪው ክፍያ በመቀበል ትምህርትን በማዳረስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከክፍያ ሂደቱ ጋርም ተያይዞ በአስተዳደሩ በተለያዩ በግል፣ በማህበረሰብ/በህዝብና በእምነት ተቋማት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ጋር ተያይዞ ጭማሪዎች ሊደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተደረገ በመሆኑና የተማሪ ወላጆች በተለያየ መንገድ ቅሬታቸውን በማቅረባቸው ችግሩን ለመፍታት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ እና የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር የየትምህርት ቤቱን ባለቤቶችና ተወካዮች ሰብስበው አወያይተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የየትምህርት ቤቱ ባለቤቶችና ተወካዮች ከተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ጋር ተያይዞ ለጭማሪው ምክንያት ነው ያሏቸውን ጉዳዮች አቅርበዋል፡፡ ትምህርት ቢሮ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች መምህራን የጄኤጂ ጭማሪ በማድረጉ የግልና መንግስት ትምህርት ቤቶች መምህራን የደምወዝ ልዩነት በመኖሩና የግል ትምህርት ቤቶች መምህራን ጭማሪ ሊደረግልን ይገባል በማለት በመጠየቃቸው፤ በሌላ በኩልም ለመንግስት ትምህርት ቤቶች መምህራን ደምወዝ ጭማሪ በመደረጉ የግል ትምህርት ቤት መምህራን ወደመንግስት ትምህርት ቤት እየተዛወሩ በመሆናቸው፤ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን ለመተግበር በሚደረገው ጥረት ተጨማሪ ክፍሎች እንዲከፈቱ ምክንያት በመሆኑና ጉዳዩም መምህራን ላይ ጫና በመፍጠሩ ይህም ትምህርት ቤቶችን ለተጨማሪ ክፍያ በመዳረጉ፤ ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞም የተለያዩ ወጪዎች በመኖሩና ሌሎች ተጨማሪ ወጪዎች ትምህርት ቤቶች በማውጣት ላይ የሚገኙ በመሆኑ በወጪዎቹ ምክንያት የትምህርት ቤቶቹ ህልውና አደጋ ውስጥ ስለሚገኝ ትምህርት ቤቶቹን ለማስቀጠል ሲባል ለተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ጭማሪ እንደምክንያት በመድረኩ ከየትምህርት ቤቶቹ ባለቤቶችና ተወካዮች ከተነሱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም የተለያዩ ጉዳዮችን ምክንያት በማድረግ ለተማሪዎች ከፍተኛ ክፍያ የሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች እና ዝቅተኛ ክፍያ የሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች በመኖራቸው የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ሁኔታው እኩል ሊታይ አይገባምም ተብሏል፡፡ በተያያዘውም በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በኮቪድ 19 ምክንያት ትምህርት ቤቶች ለሚያወጡት ተጨማሪ ወጪ ትምህርት ቢሮ ሊያግዘን የሚችልበት ሁኔታ ካለ ቢታይ በሚልም ከመድረኩ ተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡ በተያያዘም ችግሩንም ለመፍታት ትምህርት ቢሮ ወደትምህርት ቤቶች ወርዶ በአግባቡ የሚፈትሽበት ሁኔታ ቢኖር በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች እንደሌላው የቢዝነስ ተቋማት ሊታይ እንደማይገባና በዋነኝነት ዜጋን የመቅረጽ ጉዳይ ላይ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው የህዝቡን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል በማለት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆኑት ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ ተናግረዋል፡፡
የጄኤጂ ጭማሪን በተመለከተ ጭማሪው 2011 ዓ.ም የተደረገ ስለመሆኑና ይህን ታሳቢ በማድረግም የግል ትምህርት ቤት መምህራን የይጨመርልን ጥያቄ ሊያነሱ ቢችሉም መገንዘብ የሚያፈልገው ህዝቡ አሁንም ላይ በኮቪድ 19 ጫና ውስጥ ባለበት ሁኔታ የተማሪዎች የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ የህዝቡን ችግር ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ አክለውም ከጭማሪው ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች የወላጅ ኮሚቴና ትምህርት ቢሮን ሳያሳውቁ ጭማሪ ማድረጋቸው ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም መመሪያዎችን የማውጣትና ትምህርት ቤቶችን የመከታተል ኃላፊነት የትምህርት ቢሮ በመሆኑ ኮሚቴ በማዋቀር አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ከሚያስከፍሉት ክፍያና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎች ዙርያ ወደትምህርት ቤቶች በመውረድ መረጃ በመውሰድ ጥናት የሚደረግ ስለመሆኑ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
የመጽሃፍና ሌሎች መሰል የግብአት ወጪዎችን በተመለከተም የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ለግል ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና በቀጣይም ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ስለመሆኑም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ የግል ትምህርት ቤቶችን የመንግስትን ጉድለት የሚሞሉ አጋዥ አካላት አድርጎ የሚያስብ ቢሆንም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የግል ጥቅማቸውን ብቻ ታሳቢ በማድረግ የተጋነነ ጭማሪ በተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ላይ ማድረጋቸው አግባብነት የለውም ሲሉ የተናገሩት የአስተዳደሩ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ ናቸው፡፡
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች አግባብ ባልሆነ መንገድ ትርፍ ለማካበት የሚያደርጉት የተጋነነ የትምህርት ክፍያና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎች የነዋሪውን የኑሮ ሁኔታና አሁን ላይ ያለውን የኮቪድ 19 ጫና ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ነው በማለት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁኃር ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ትምህርት ቤቶችን በአግባቡ ከመከታተልና ከመቆጣጠር አንጻር ትምህርት ቢሮ የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡ በቀጣይ ህዝቡ ላይ የኮቪድ 19 ተጽዕኖ ባገናዘበ መልኩ ትምህርት ቢሮ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከተማሪዎች የክፍያና ተያያዥ ሁኔታዎች ጋር የሚያደርገውን ጥናት መነሻ በማድረግ መመሪያ እንደሚወጣና የክፍያ ሁኔታም በዚሁ መመሪያ የሚመራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች በኩል የሚስተዋለውን የመምህራን ችግርን ለመፍታት ከመምህራኑ ጋር በመቀራረብና በማወያየት መስራት ያስፈልጋል በማለት አቶ ከድር አሳስበዋል፡፡


