በድሬዳዋ አስተዳደር የበልግ ወቅት የዝናብ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የተሰጠ ቅድመ ማስጠንቀቂያ::

    ድሬዳዋ 2 የዝናብ ወቅቶች፣ ማለትም ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ግንቦት መጨረሻ የሚኖረው (የበልግ የዝናብ ወቅት) እና ከሀምሌ መጀመሪያ እስከ መስከረም አጋማሽ የሚኖረው (የክረምት የዝናብ ወቅት) እንዳሏት ይታወቃል::
    በየወቅቶቹ በአስተዳደሩና በአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች በሚዘንበው ዝናብና በሚፈጠረው ደራሽ ጎርፍ ሳቢያ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሰዎች ላይ የሞት፣ በንብረት ላይ ውድመት፣ እንዲሁም በእለት ተእለት የህብረተሰቡ የአኗኗር ሂደት ላይ ጉዳት ሲያስከትል ቆይቷል::
    እስካሁን በተለያዩ ጊዜያት፣ ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ እና ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች በመሰጠታቸው፣ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በእጅጉ ለመቀነስ ተችሏል::
    በዚህ የበልግ የዝናብ ወቅት፣ ማለትም ከሚያዝያ አጋማሽ እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ፣ ከመደበኛ ጋር ተቀራራቢ የሆነ የዝናብ መጠን ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ::
    ባለፉት ሳምንታት በአስተዳደሩ የዘነበው ዝናብ፣ ለጎርፍ መከሰት ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ፣ በከተማ እና በገጠር አካባቢዎች፣ የጎርፍና ተያያዥ አደጋዎች ተከስተዋል፣ በቀጣይም ሊከሰት እንደሚችል ይገመታል::
    በመሆኑም፣ በአስተዳደራችን ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመቋቋም፣ የመንግስት እና የግል ተቋማት እንዲሁም መላው ነዋሪዎች፣ እነዚህን የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊተገብሩ ይገባል::
    1ኛ- ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ የጎርፍ መሄጃ መንገዶች አካባቢ የሚኖሩና የሚንቀሳቀሱ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ያረጁ ቤቶች፣ ህንፃዎች፣ የግንብ አጥሮች እና ሌሎች ግንባታዎች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ::
    2ኛ- ሁሉም አካላት በአካባቢያቸው የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮችን ማፅዳትና ተጨማሪ ማዘጋጀት፣ እንዲሁም የተለያየ መጠን ያላቸውን የጎርፍ መከላከያ ስራዎችን በስፋት ማከናወን::
    3ኛ- በየወቅቱ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት፣ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚተላለፉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን፣ በንቃት መከታተልና በአግባቡ መተግበር::
    4ኛ- በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኙ ህፃናት እና አረጋውያን፣ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው እንዳይሄዱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ::
    እንዲሁም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የዘነበውን ዝናብ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ለግብርና ስራ፣ ለእርሻና ውሀ ማቆር አገልግሎት በማዋል ተጠቃሚ መሆን ይገባል::
    “ለአደጋ የማይበገር ማህበረሰብ በጋራ እንገንባ!”
    በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የድሬዳዋ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት