በቅድሚያ ለመላው የአስተዳደራችን እንዲሁም የሃገራችን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ ፤ ቅዱሱን የረመዳን ወር በሰላምና በመደጋገፍ አሳልፋችሁ ፤ የፍቅርና የአብሮነት መገለጫ ለሆነው 1,442ኛው ታላቁ የኢድ አልፈጥር በዓል እንኳን በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ፤ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ።
ኢድ ሙባረክ !
የጾም፣ የፀሎትና ከፈጣሪ ጋር የመገናኛ የሆነውን ቅዱሱን የረመዳን ወር ከክፉ ምግባር በራቀ መንፈሳዊ ምግባር እንዲሁም ባህላችን በሆነው መተዛዘንና መረዳዳት አሳልፋችሁ ታላቁን የኢድ- አልፈጥር በአል በሰላም ለማክበር ስለበቃችሁ በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ ።
በአሉን ስናከብር በረመዳን ወር ስናደርግ እንደነበረው ሁሉ ከግል ጉዳያችን ባሻገር ስለ ሀገራችን ሰላምና አንድነት በማሰብ ፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ ያዘኑትን በማፅናናትና በፈጣሪ ፊት የሚወደደውን መልካም ነገር ሁሉ
በመፈፀም እንዲሆን አደራ ለማለት እፈልጋለሁ።
የምንገኝበት ጊዜ የውጪና የውስጥ ጠላቶች በመቀናጀትና በመናበብ የአገራችንን ህልውና እየተፈታተኑ የሚገኙበት ፈታኝ ወቅት መሆኑ ለሁላችንም ግልፅ ነው።
በመሆኑም የሚገጥሙንን መሠናክሎች በጥበብና በብልሃት በማለፍ፤ ሠላማችንን ጠብቀን ፍቅርና አንድነታችንን በማጠናከር ፤ የበለፀገችና ለነዋሪዎቿ የምትመች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንድንቆም በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ።
በአሉን ስናከብር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም፣ ርቀታችንን በመጠበቅ ፣ ከመጨባበጥና ከንክኪ ተቆጥበን በአስጊ ሁኔታ ጉዳት እያስከተለ ከመጣው የኮረና ወረርሽኝ እራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን ለመጠበቅ ተጠንቅቀን እንዲሆንም ለማስታወስ እወዳለሁ ።
በመጨረሻም በአሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የአንድነት በአል እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ፡፡
ኢድ ሙባረክ!!
መልካም በአል!!
ግንቦት 4/2013 ዓ.ም
ድሬዳዋ


