የኢድ አልፈጥር በአል ሲከበር ያለው የሌለውን በመርዳት እንዲሁም በፈጣሪ ዘንድ የሚወደዱትን ተግባራት በመፈፀም ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

    1442 ተኛው የኢድ አልፈጥር በአል በድሬዳዋ አስተዳደር የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
    በድሬዳዋ አስተዳደር የኢድ አልፈጥርን በአል ለማክበር ከማለዳው 12 ሰዓት አንስቶ የእምነቱ ተከታዮች በከተማው በሚገኘው የኢድ ሰላት መስገጃ ስፍራ በሚያመሩበት ወቅት ተከቢርታ ወይም የአላህን ትልቅነት በማውሳት ወደ መስገጃ ስፍራው አምርተዋል፡፡
    በኢድ ሰላት መሰገጃ ላይም በመገኘት ለእምነቱ ተከታዮች መልእክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ በተለይም የኢድ አልፈጥር በአል ሲከበር በረመዳን ፆም ወቅት ሲደረግ የነበረውን ያለው የሌለውን የመርዳትና የመተጋገዝ እንዲሁም በፈጣሪ ዘንድ የሚወደዱትን ተግባራት በመፈፀም ሊሆን እንደሚገባ ተናግረው ከዚሁ ጋር ተያይዞም ስለ ሀገራችን ሰላምና አንድነት በማሰብ በአሉን ሊያከብሩት እንደሚገባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ተናግረዋል፡፡
    የእስልምና ሀይማኖት የመቻቻልና የመከባበር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በኢድ አልፈጥር በዓል ወቅት የተቸገሩትን በመርዳትና በአንድነት በአሉን ሊያከብሩት እንደሚገባ የድሬዳዋ አስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ መሀመድ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡
    በተለይም የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ከመኖሪያ አካባቢ አንስቶ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የከተማው ነዋሪዎች በመርዳትና በመለገስ በአሉን በደስታ እንዲያከብሩት ማድረግ እንደሚገባ የእምነቱ ተከታዮች የሆኑት የከተማው ነዋሪዎች ተናግረው ከበአሉ ጋር ተያይዞም የከተማው ነዋሪዎች ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት በመሆንና ሰላማቸውን በማስጠበቅ በአሉን ሊያከብሩት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡