በድሬዳዋ አስተዳደር በሞባይል በአፕሊኬሽን ሶፍትዌር በመታገዝ የሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ሊጀመር ነው ።

    ኤልኔት ኢንጂነሪንግ ፒኤልሲ ስር ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ ኩባንያዎች አሉ እነዚህም ዘጠኝ ኩባንያዎች ሙሉ ለሙሉ ሀገር በቀል ኩባንያዎች ሲሆኑ ንብረትነታቸውም የኢትዮጲያዊያን የሆኑ ድርጅቶች ናቸው ። በዋናነትም ድርጅቶቹ የሚሰሩትም የማህበራዊ አገልግሎትን መሰረት ያደረገ ቢዝነሶችን ሲሆን ኤልአውቶ አሴምብሊንግ የተባለው ኩባንያ ቼሪና ጃክ የተባሉ ብራንድ መኪናዎችን በማስመጣትና በመገጣጠም ይሸጣል ። ከዚህ ባለፈም ኤል ታክሲ ” ታክሲዬ ” በሚል ስያሜ ብራንድ የሆኑ የሜትር ታክሲ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን ታክሲዬ ድራይቨር አፕሊኬሽኖችን በመጠቀምም አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ።
    ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ ፒኤልሲ አውሮፓ ሰራሽ መኪኖች ወደ ሀገራችን ኢትዮጲያ ብሎም ወደ ከተማችን ድሬዳዋ መኪናዎችን በማስመጣትና በመገጣጠም በቀላሉ በሞባይል ስልካችን በመጠቀም የትራንስፖርት አገልግሎት በመጠቀም በተለይም ለከተማዋ ነዋሪዎች በእጅጉ እንደሚጠቅምና ከተማ አስተዳደሩም ከድርጅቱ ጎን መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
    ድርጅቱ በተለይም ከቀረጥ ነፃ የሆኑ ዘመናዊ ታክሲዎችን ወደ ሀገራችን ብሎም ከተማችን ድሬዳዋ ላይም በማስመጣትና የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከዚህ ቀደም በከተማዋ ላይ ያለውን የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎትን ሊያሻሽል የሚችልና ለወጣቶችም ጭምር የስራ እድልን ሊፈጥር እንደሚችል የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ አብዱጁዋድ መሀመድ ተናግረው ይሄም ድርጅት በከተማዋ ላይ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ለመሰማራት እያደረጉት ያለውንም እንቅስቃሴ አድንቀው በቀጣይም በዚህ ዘርፍ ላይ የግል ባለሀብቶችም ሆኑ የከተማው ነዋሪዎች መሰማራት እንደሚችሉም ነው አቶ አብዱጁዋድ የተናገሩት ።
    ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ ፒኤልሲ በከተማችን ድሬዳዋ ላይ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱን በመክፈት ለግል የትራንስፖርት ታክሲ አገልግሎት የሚውሉ መኪናዎችን በማስመጣትና በሶፍትዌር አፕሊኬሽን በመታገዝ የሜትር ታክሲ አገልግሎት በመስጠት በተለይም ከተማዋን በትራንስፖርቱ ዘርፍ ወደ ዘመናዊ አሰራር ከመለወጡም ባለፈ በከተማዋ ላይ ያለውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍና ለወጣቶችም የስራ እድል እንደሚፈጥር የኤል አውቶ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በቀለ አበበ ተናግረው በቀጣይም በማኑፋክቸሪንግና በንግድ ዘርፍ ላይም በከተማዋ እንደሚሰማሩም ነው የተናገሩት ።
    በዝግጅቱ ላይ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል ።