የድሬዳዋ ከተማ በሁለንተናዊ መነቃቃት ላይ እንደምትገኝ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ገለፁ፡፡

    ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
    አቶ ሮቤል በተለይ ለወጋሕታ ጋዜጣ እንዳስታወቁት፣ ድሬዳዋ ከኢንዱስትሪ ጋር የቆየ ትስስር ያላት ከተማ ናት፣ ኅብረተሰቡም የዚህ ባህልና ልምድ ያለው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የብዙ ኢንቨስመንቶች መዳረሻ እየሆነች ነው።
    የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ተከትሎ ብዛት ያላቸው ኢንዱስትሪዎች በከተማዋ እየተገነቡ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሮቤል፣ ይህም ለከተማዋ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለከተማዋም መነቃቃት ፈጥሯል ብለዋል፡፡
    ድሬዳዋ ኮቪድ 19 ፈተና ከሆኑባቸው ከተሞች አንዷ በመሆኗ ብዙ የህክምና ማእከላትና የማቆያ ስፍራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው ፤ ኮቪድ 19 በድሬዳዋ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል። ጫናውን ለመቀነስም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደተሰሩም አስታውቀዋል፡፡
    ወረርሽኙን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በመከላከል ምርታማነትን ማስቀጠል ይቻላል በሚል ወደ ሥራ መገባቱን ያመለከቱት አቶ ሮቤል፣ እስካሁን ባለው አፈጻጸምም ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
    የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከባብረው በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ያመለከቱት አቶ ሮቤል፣ በቀድሞ የፖለቲካ ሁኔታ በሃይማኖትና በብሔር ግጭቶች በመቀስቀስ ሰፊ የሚባል የሰላም መደፍረስ እየተስተዋለ እንደቆየ በማስታወስ ከዚህ ጋር ተያይዞ በፀጥታ ዙሪያ ሰፊ ሥራ መሰራቱን ገልፀዋል። በዚህ ሂደት ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በመለየት የተሻለ የጸጥታ መዋቅር በመገንባትና ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይቶች በማድረግ ውጤት የተገኘበት ሥራ መሰራቱንም ገልፀዋል፡፡
    ምርጫን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ብዙ ምርጫዎች እንደተደረጉ የጠቆሙት ኃላፊው ፤ይሁን እንጂ ምርጫዎቹ ነፃ፣ ፍትሃዊና በብዙሃኑ ታማኝነት ላይችግር እንደነበረባቸው ገልፀው ፤ ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
    ድሬዳዋ ላይ ብልፅግናን ጨምሮ ዘጠኝ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳሉ ያስታወቁት አቶ ሮቤል፣ መራጩ ሕዝብ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የምርጫ ካርድ በስፋት እየወሰደ እንደሚገኝና ከዚህ በፊት ከነበረው እንቅስቃሴ አሁን የተሻለ እንደሆነ አመልክተዋል። ከተማዋ ከለውጡ በኋላ የምትተዳደርበትን ቻርተር ለመቀየር ከሕዝብ ጋር ውይይት መደረጉንና የከተማዋን እድገት በሚያፋጥን መልኩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
    ድሬዳዋ ከለውጡ በፊት በሁለት ፓርቲ ስትመራ የቆየች ከተማ እንደሆነች ፣ ከለውጡ በኋላ ግን አንድ ውህድ ፓርቲ ስለተፈጠረ የከተማችን ጉዳይ በሚመለከት በአንድነት የምንወስንበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል። ይህም በከተማዋ ላይ መነቃቃት መፍጠሩንም አቶ ሮቤል አስታውቀዋል፡፡
    ፎቶ ፋይል