የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ተጠናቀቀ::

    650 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኃይማኖት አባቶችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ግድቡን በተመለከተ ዛሬ ውይይት አድርጓል፡፡
    በዚህ ውይይት ላይ የኃይል መሥመር ዝርጋታው ከግድቡ ከተገነባበት ጉባ አንስቶ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት እስከሚገኝበት ሆለታ ድረስ ተዘርግቷል ተብሏል፡፡
    የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል ዶክተር በለጠ ብርሃኑ፣ አሁን ላይ ከግንባታና ከኮንክሪት ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚሰራው የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራ 91.8 በመቶ መድረሱን ነው የጠቆሙት፡፡
    የግድቡ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው 54.5 በመቶ እንዲሁም የኃይድሮሊክ ስትራክቸር ደግሞ 55.2 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
    ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት፡፡
    በተጓዳኝም የግድቡ ሁለት ተርባይኖች የቅድመ ኃይል ምርት በመጪው ክረምት መጨረሻ አካባቢ እንደሚጀምርና ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዶክተር በለጠ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡