ለኤች አይቪ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ምርመራ እንዲያገኙ ቫይረሱ ከተገኝባቸውም ወዲያውኑ ህክምና እንዲሁም መድሃኒት መጀመር የሚያስችል መርሃ ግብር / RoTA / ዘመቻ እንደ ድሬደዋ አስተዳደር እየተተገበረ ይገኛል::
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ እነደ አገርም ሆነ እንደ ድሬደዋ የኤች አይቪ ስርጭትን ከመከላከል አንጻር መቀዛቀዝ መኖሩን ገልጸው ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ታሳቢ ያደረገ መረሃግብር ተዘጋጅቶ ከስድስት ወር በፊት በዘመቻ መልክ ወደስራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡
በድሬደዋ ደረጃ የመረሃ ግብሩ የስድስት ወር አፈፃፀም መገምገሙን የገለፁት የቢሮ ሃላፊዋ አገልግሎቱን ከመስጠት እረገድ የባለሙያ እጥረት መኖር ፤ ህብረተሰቡ በፍቃደኝነት ላይ ተመሰረተ የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራ የማድረግ ውስንነት መኖርን ጨምሮ ከበጀትና ሌሎች ተያያዥ ክፍተቶች መስተዋላቸውን በግምገማው ተመላክቷል ብለዋል፡፡ ያሉችግሮችን ተቀርፈው በመረሃ ግብሩ ለማሳካት የተቀመጡ ግቦች ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ወ/ሮ ለምለም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የማይታይ መጠን = የተገታ መተላለፍ << በደሜ ውስጥ ያለውን የኤች አይ ቪ ኤድስ መጠን በመቆጣጠር ፤ስርጭቱን እገታለሁ >> በሚል መሪ ቃል ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለ የማህበረሰብ ክፍሎች እራሳቸውን ጠብቀው ሌሎችን በቫይረሱ እንዳይያዙ ለማስቻል ያለመ መረሃግብር ዘመቻ በግምገማ መድረኩ ይፋ መደረጉን የቢሮ ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
አክለውም በተለይ ወቅታዊው የኮሮና ወረሽኝ ለየኤች አቪ ኤድስ የሚሰጠውን ትኩረት እንዳያዳክመው የሁለቱም መረሃ ግብሮች ዘመቻ ተግባራዊ መሆን አስተዋጾው ከፍተኛ እንደሆነ ወ/ሮ ለምለም አብራርተዋል፡፡በግምገማ መድረኩ ከኤች አይ ቪ አገልግሎት አሰጣጥ እረገድ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ሆስፒታሎች እውቅናና ሽልማት ተበርክቷል፡፡


