የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ 1999 ዓ.ም ከተቋቋሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ሲሆን በተለይም ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ በርካታ ስራዎችን ከመስራት በዘለለ በ 2030 ከአፍሪካ ምርጥ 10 የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለማድረግ በመሰራት ላይ ይገኛል ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል ፍትህና ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመተባበር 5 ተኛው ዙር የኢትዮጲያ ህግ ትምህርት ቤቶች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ተካሂዷል ።
በውድድሩ መዝጊያ ስነ-ስርአት ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ኡባህ አደም በተለይም የዩኒቨርሲቲው ህግ ኮሌጅ ከድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ ህግ ጉዳዮች ጋር በጋራ በመተባበር የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረው የፌዴራል ፍትህና ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ለመስራት ላሳዩት አብሮነት አመስግነው በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ እንደሚሰራም ነው ዶክተር ኡባህ አደም በእለቱ የተናገሩት ።
ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር የህግ እውቀት በተግባር የሚፈተሽበት ብቻ ሳይሆን በርካታ ማህበራዊና ሌሎች ጠቀሜታዎችም ያሉት ሲሆን ይህም ታላቅ አመታዊ ሁነት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተሳታፊ የሆኑ ተማሪዎች ፣ መምህራን እንዲሁም ዲኖች የሚሰባሰቡበትና የሚታደሙበት በመሆኑ አንዱ ከሌላው የተለያዩ ልምዶችን የሚካፈልበትና የሚቀስምበት መሆኑን የፌዴራል ፍትህና ህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ምትኩ ማዳ ተናግረው ይህም ሁነት አንዱ የሌላውን ባህልና ልምድ የሚረዳበትና የሚቀስምበት በመሆኑ ህብረ-ብሄራዊነትም እንደሚጎለብት አቶ ምትኩ ተናግረዋል ።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተከታታይ 4 ቀናት ሲካሄድ በነበረው 5 ተኛው ዙር የኢትዮጲያ ህግ ትምህርት ቤቶች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ላይ 1 ኛ ጎንደር ፣ 2 ኛ ባህርዳር ፣ 3 ኛ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሆነው ውድድሩን ያጠናቀቁ ሲሆን ለውድድሩ መሳካትም የላቀ አስተዋፆ ለነበራቸው አካላትም እውቅና ተሰጥቷል ።


