በ 6 ተኛው ሀገራዊ ምርጫ በድሬዳዋ አስተዳደር 9 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ፡፡ ሀገራዊ ምርጫውም ከመካሄዱ በፊት በምርጫው ላይ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መድረክ በማመቻቸት ፖሊሲያቸውን ለምሁራ ለነዋሪዎች ብሎም ለደጋፊዎቻቸው ሀሳባቸውን ያቀርቡ ዘንድ መድረክ አመቻችቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው መድረክ ላይም ብልፅግና ፓርቲ ፣ እናት ፓርቲ ፣ ኢዜማ ፓርቲ ፣ አብን ፓርቲ እንዲሁም ኢ.ሶ.ዴ.ፓ ፓርቲ ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ፣ ለባለድርሻ አካላት ፣ ለፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ለተጋባዥ እንግዶች ያላቸውን የፖሊሲ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ተደርጓል ፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተፎካካሪ ፓርቲ ባዘጋጀው መድረክ ላይም በዋናነት የትምህርት ፖሊሲና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ያላቸውን የፖሊሲ አጀንዳዎች ለ 22 ደቂቃ ያህል ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ያቀረቡ ሲሆኑ በነዚህም አጀንዳ ላይ ሰፊ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር በ 6 ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የሚወዳሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉንም ሊያግባባ በሚችልባቸው ሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ሀሳባቸውንና ፖሊሲያቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ታልሞ መድረኩ መዘጋጀቱን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ተናረዋል፡፡
6 ተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ አግባብ ይካሄድ ዘንድ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የራሱን ድርሻ ማበርከት ስላለበት በምርጫው ላይ ተሳታፊ ለሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ በማዘጋጀት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለሚመርጣቸው ማህበረሰብ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ለማድረግ እንደተዘጋጀ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር መገርሳ ቃሲም ተናግረው እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲም ባሉበት አካባቢ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚህ አይነት መሰል መድረኮችን በማዘጋጀት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ መደረግ እንደሚገባና በቀጣይም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መሰል መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ዶክተር መገርሳ ቃሲም በእለቱ ተናግረዋል፡፡


