ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ለአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኦክሲጂን ሲሊንደርና ተያያዥ ግብአቶችን ድጋፍ አድርጓል ።

    በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 35 ሺህ 499 ላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 5 ሺህ 231 የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የ 82 ሰዎች ህይወትም አልፏል ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በድሬዳዋ አስተዳደር በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ የሚያዙ እንዲሁም ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ለታማሚዎች የሚሆን የኦክስጅን እጥረትም እያጋጠመ ይገኛል ።
    ይህንንም ከግምት ውስጥ ያስገባውና በድሬዳዋ አስተዳደር በበርካታ የበጎ አድራጎቶች ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ለአስተዳደሩ ጤና ቢሮ የኦክሲጂን ሲሊንደርና ተያያዥ የህክምና ግብአቶችን ድጋፍ አድርጓል ።
    በድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር በተለይም የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ በድሬዳዋ አስተዳደር ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ተከታታይ የሆኑ ድጋፍ ማድረጉም በዘለለ የተለያዩ ማህበራዊ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ሌሎችም ባለሀብቶችና ድርጅቶች መሰል ድጋፎችን ሊያደርጉ እንደሚገባም አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል።
    በአስተዳደሩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋበትና የኦክሲጅን ድጋፍ በሚያስፈልግበት ወቅት ናሽናል ሲሚንቶ ከአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ጎን በመሆንና ድጋፍ በማድረግ ላሳዩት ትብብር የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወሮ ለምለም በዛብህ አመስግነው አሁን ላይም ከ 100 በላይ የኦክስጂን ሲሊንደሮችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረጋቸውም በዘለለ በየሳምንቱ 20 የኦክሲጅን ሲሊንደሮች ሙሌት ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባታቸውም ለፋብሪካው አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
    የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግስ ኩባንያ ቦርድ ሊቀመንበርና ባለቤት በሆኑት በ ዶ\ር ቡዙአየው ታደለ ስምና በናሽናል ሲሚንቶ ስም በቀጣይም አቅም በፈቀደ ሁሉ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና በአስተዳደሩ ለሚሰሩ የልማት ስራዎችም ከአስተዳደሩ ጎን እንደሚቆሙም የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይና የማርኬቲንግና ሴልስ ሀላፊ የሆኑት አቶ አዳነ አለሙ ተናግረዋል ።
    የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ለአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኦክሲጂን ሲሊንደርና ተያያዥ የህክምና ግብአቶችን በፈረንሳይ ሆስፒታል በተደረገው የድጋፍ ስነ-ስርአት ላይ አስረክቧል ።