በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስተባባሪነት ከዘጠኝ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የስርአተ ምግብ ተጠሪዎች በገጠር ቀበሌዎች ያለውን የስርአተ ምግብ ኮሚቴዎችን ለማጠናከርና በትምህርት ቤቶች ያለውን የምገባ ስነ ስርአት አስመልክቶ ድጋፍና ክትትል ተግባር አከናውነዋል።

    የስርአተ ምግብ ተጠሪዎች በጀልዴሳ ክላስተርና በቢያአዋሌ ክላስተር ለሁለት ተከታታይ ቀናት ባደረገው ምልከታ በገጠሩ በስርአተ ምግብ ዙሪያ የተቋቋመው ኮሚቴ በሙሉ ቁመናው ወደ ተግባር ባለመግባቱ እየተከሰተ ያለውን የመቀንጨር ችግር እንዳይባባስ ኮሚቴው ጊዜ ሳይሰጥ ወደ ስራ መግባት እንዳለበትና ባለድርሻ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በምግብ እጥረት ምክንያት እየተከሰተ ያለውን የመቀንጨር ችግር ላይ ርብርብ በማድረግ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
    ኮሚቴው በጀልዴሳና በብያዋሌ ክላስተር የምገባ ስነ ስርዓት የሚካሄድባቸውን ትምህርት ቤቶች ተዟዙሮ የተመለከተ ሲሆን በትምህርት ቤቱ የሶላር ፊውዝ በመቃጠሉ ምክንያት የውሀ እጥረት በመከሰቱ ችግር እንደገጠማቸው የለገዲህ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ር/መምህር አሚር አህመድ በመግለፅ የምገባ ኘሮግራሙን በሳተላይት ትምህርት ቤት ለማካሄድ የማብሰያና የመመገቢያ እቃዎች እጥረትም እንደገጠማቸው ጨምረው ገልፀዋል።
    በተመሳሳይም የጀልዴሳ ክላስተር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የቢሻን በሂ ትምህርት ቤት በተለያዩ ምክንያቶች የውሀ እጥረት መኖሩን ር/መምህራኖች ተናግረዋል።
    በትምህርት ቤቶች የምገባ ኘሮግራም መጀመሩ በችግር ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩና እንዳያቋርጡ አድርጓል ሲሉ የትምህርት ቤቶቹ ር/መምህራን ተናግረዋል።
    የምገባ ኘሮግራሙ የአካባቢው ማህበረሰብ በማብሰል እንደሚተባበሩ ር/መምህራኖቹ ገልፀዋል።
    በገጠሩ ማህበረሰብ የደረሠውን የምግብ እጥረት ዋና ምክንያት ናቸው ያሉትን የአካባቢው ማህበረሰብ ሲገልፁ በዋንኛነት የማህበረሰቡ የስራው ባህል ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑ እና የሚደረጉ የእርዳታ ድጋፍ ወቅቱን የጠበቀ አለመሆኑ ይገኙበታል።