አሜሪካ በኢትዮጲያ ላይ የጣለችውን ማእቀብ ተከትሎ የሚፈጥረው ተፅእኖ ላይ የሚመክር ውይይት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል ።

    ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሀገራችን ኢትዮጲያ እያከናወነችው ባለችው የልማትና የህግ-ማስከበር ስራዎች ብሎም የውስጥ ጉዳዮች ላይ የአሜሪካ መንግስት ሀገራችን ላይ ማእቀብን ጥሏል ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የአሜሪካ ማእቀብ በኢትዮጲያ ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ምሁራን በተገኙበት ውይይት አካሂዷል ።
    በዚሁም ውይይት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀው መደረክ ላይ የሚደረገው ውይይት በተለይም ለሀገር በሚጠቅምና የተሻለ ሀሳቦችን በማንሳት ውይይት እንደሚደረግና በቀጣይም መሰል የውይይት መድረኮች በዩኒቨርሲቲው እንደሚዘጋጅም ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል ።
    ሀገራችን ላይ በርካታ ዩኒቨርሲቲ እንደመኖሩ መጠን ቡዙ ምሁራን ስለሚኖሩ ሀገራችንን ሊጎዳ የሚችል እንደዚህ አይነት ማእቀብ ሲጣሉ እንደ ዩኒቨርሲቲ ለጉዳይ ትኩረት በመስጠት ለመንግስት ምሁራዊ ሀሳብ የመስጠትና የመደገፍ ብሎም በሀገራችን ላይ የተከሰተውን ጉዳይ በውጪ ሀገር ብሎም በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ማህበረሰብ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የማሳወቁ ሁኔታ ዙሪያ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ላይ ቡዙ ስራዎች ስለሚጠበቁ እንደዚህ አይነት አጀንዳዎች ላይ መወያየቱ ሊበረታታ እንደሚገባ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር መገርሳ ቃሲም ተናግረዋል ።
    በውይይቱ ላይም ተሳታፊ የሆኑት የዩኒቨርሲቲው መምህራን በበኩላቸው ተማሪዎቻቸው የሀሰት መረጃን እንዳያሰራጩ እንዲጠነቀቁ ማሳወቅ እውነታውንም በተገኘው አጋጣሚ ለአለም ህዝብ ማሳወቅ እንዲገባ ተናግረው ምሁራንና መምህራን ብሎም ማንኛውም ኢትዮጲያዊ የውስጥ አንድነታችንን ልዩነታችንን ብሎም አብሮነታችንን ማስጠበቅ እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተናግረዋል ።