የድሬዳዋ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋር በመተባበር ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል ።

    የሳይንስና ቴክኖሎጂን አዋጪነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር አቀፍ ደረጃ አደረጃጀት ተፈጥሮለት በክልሎችና በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሀገር አቀፍን አቅጣጫ በመከተል የተቋቋመ ሲሆን በዚህም እንደ ሀገር ሰፊ የሆኑ ስራዎች ከመሰራታቸውም በዘለለ በአሁን ሰአት በከተማችን ድሬዳዋም የሀገር አቀፍን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተቋቁሞ ወደ ተግባር በመግባት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ።
    ከዚሁ ጋር ተያይዞም የድሬዳዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የ 2013 እና የ 2014 የእቅድ አፈፃፀም እንዲሁም እንደ ሀገር ከታቀደው የ 10 አመት የልማት እቅድ ውስጥ ቴክኖሎጂንና ኢኖቬሽን በተመለከተ በምን አግባብ መጔዝ እንዳለበት እንዲሁም አደረጃጀቶቹስ በምን አግባብ መጠናከር እንዳለባቸውና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማድረግ ያለበትን ድጋፍና በቀጣይ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል ።
    በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ የድሬዳዋ አስተዳደር ያሉበትን ችግሮች ለማቃለልና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ መሳሪያ የሆነውን የሳይንስ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች በመጠቀም ረገድ በጅምር ላይ መሆኑን ተናግረው ይህ ዘርፍ በሀገር ደረጃ ብሎም የአስተዳደራችንን ነዋሪዎች የተሻለ ኑሮና ኢኮኖሚ የሚያጎናፅፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁሉም የበላይ ሀላፊዎች ፣ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ፣ በተለያዩ የምርምር ዘርፍ የተሰማሩ ተቋሞች ፣ የግል ባለሀብቶችና ተማሪዎች በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ አህመድ ተናግረዋል ።
    ሀገራችን አሁን ላይ የጀመረችውን የእድገትና የብልፅግና ጉዞ ስኬታማ ይሆን ዘንድ የምርምር ተቋሞቻችን ቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር ከመስራታቸው ባለፈ ስራ ፈጠራን በማበረታታት በቴክኖሎጂም መደገፍ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ዶክተር ፎዚያ አሚን ተናግረው መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚን ከመገንባት አንፃር የ 10 አመት የልማት እቅድ እንደያዘና ለዚህም መሳካት ሁሉም አካላት በጋራ በመሆን በመስራት ማሳካት እንደሚገባ ዶክተር ፎዚያ በእለቱ ተናግረዋል ።
    በፕሮግራሙ ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሀሩን አብዱረህማንን ጨምሮ የተለያዩ ቢሮ ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።