የአሸባሪውን የህውሀት ጁንታ ቡድን ሀገርን የማፈራረስና የመበታተን የሽብር ተግባርና ተልእኮ የማምከንና ህግን የማስከበር ሀገራዊ ጥሪን ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ልዩ ሀይሎች ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለዋል ። ይህንንም ሀገራዊ ጥሪ በመቀበልም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የልዩ ሀይሎች በሀገራዊው የህግ የማስከበር ዘመቻ ለሚሳተፉ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ሀይል አባላት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና የካቢኔ አባላቶቻቸው፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በተገኙበት ሽኝት ተደርጎላቸዋል ::
በዚሁ የሽኝት መርሀ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ሀይል የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ በዘለለ ለሀገራዊ ጥሪው በአንድነት እንደቆመና ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከልዩ ሃይል ጎን እንደሆነና በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ አስታውቀዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ሀገራችን ኢትዮጲያ የጠራችውን ታሪካዊ ጥሪ በመቀበልና የሀገራችንን ሰላም ለመጠበቅና ፣ የህዝቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ፣ የተጀመሩ ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ እድገቶችም እንዲቀጥሉ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በጥሪው ላይ መሳተፍ እድለኛነትም ከመሆን ባለፈ ክብር መሆኑን ድሬዳዋ አስተዳዳር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረው የአስተዳደሩ ልዩ ሀይልም ኢትዮጲያዊነቱን ማእከል በማድረግ የሚፈለገውን ግዳጅ ከመቀበል አንስቶ ግዳጁን በሚፈለገው ውጤት በማስጠበቅ ሀገራችንን ኢትዮጲያ በከፍታ ማማ ላይ ለማስቀመጥ መዘጋጀቱንም ነው ኮሚሽነር አለሙ መግራ የተናገሩት ።
የሀገራችንን ጥሪ በመቀበል መሳተፍ በራሱ ጀግንነት ነውና ይህንንም ሀገራዊ አደራ በመቀበል በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ በጀግንነት የሚጠበቅባቸውን ግዳጅ በመወጣት በድል እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሙሳ ጣሀ ገልፀዋል ።
የልዩ ሃይል አባላቱ በበኩላቸው በተሰማሩበት የሰላምና የፀጥታ ማስከበር ቦታዎች ላይ በታማኝነትና በቅንነት ግዳጃቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል ።
በሽኝት ፕሮግራሙ ላይም ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ ኡጋዞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን የልዩ ሀይሉ አባላትም ከክብር እንግዶች እጅ የሀገራችን ኢትዮጲያን ሰንደቅ አላማ በክብር ተረክበዋል ።


