ባዲቦ ማኑፋክቸሪንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊትና ለድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ሀይል የ 1.5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ ።

    ሀገራችን ኢትዮጲያ በውጪና በውስጥ ጠላቶች የተደቀነባትን አደጋ ተጋፍጣና አሸንፋ ለመውጣት ይቻል ዘንድ መላ የሀገራችን ህዝብና መንግስት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን የድሬዳዋ አስተዳደርም የልዩ ሀይሉን ፖሊስ ለህግ ማስከበር ተልእኮ ከማሰማራቱም ባለፈ የከተማው ነዋሪዎችም ዘርፈ-ብዙ አስተዋፆዎችን ባመወጣት ላይ ይገኛሉ ።
    ከዚሁ ጋር ተያይዞም በኢኮኖሚው ዘርፍ የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ ድሬዳዋን ጨምሮ በሌሎች የሀገራችን ክልሎች ትላልቅ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በመሰማራት የበኩሉን አስተዋፆ በማበርከት ላይ የሚገኘው ባዲቦ ማኑፋክቸሪንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊት የአንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ሀይል የአምስት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል ።
    የባዲቦ ማኑፋክቸሪንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊትና ለድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ሀይል ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪም በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ ወጣቶች የስራ እድልን ለመፍጠር በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝና ከምንም በላይ ግን የሰላም ጥቅሙ የጎላ ነውና ሀገራችንም ሰላም ትሆን ዘንድ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ሚና መወጣት እንደሚገባ የባዲቦና ማርማ ማኑፋክቸሪንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማርኬቲንግ ማናጀር የሆኑት አቶ ሚካኤል ወልዴ ተናግረዋል ።
    በድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይም የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ባዲቦ ማኑፋክቸሪንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላደረገው ድጋፍ በድሬዳዋ አስተዳደርና በፀጥታ ምክር ቤቱ ስም ምስጋናቸውን አቅርበው ሌሎች ባለሀብቶችም መሰል ድጋፎችን ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው አቶ ከድር ጁሀር የተናገሩት ።
    የተደረገው ድጋፍ የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ሰራዊትን ብሎም የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ሀይልን የበለጠ የሚያነቃቃ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረው ድጋፍ ሰራዊቱን ከዚህ በኋላም ቢሆን የበለጠ ለግዳጅ ዝግጁ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል ።