የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የህይወት ዋጋ በመክፈል ሲሰሩ ለነበሩ የጤና ባለሙያዎች እና የክብካቤ ሰራተኞች የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም ተካሄደ::

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የጤና ባለሞያዎች የደረሰባቸውን ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት የአለም ጤና ድርጅት የዘንድሮውን አመት የጤና ባለሞያዎችና ጤና እንክብካቤ ባለሞያዎች አመት እንዲሆን በወሰነው መሰረት የጤና ሚኒስቴርም ይህንኑ ከሐምሌ 11-17 የጤና ባለሞያዎችና ጤና እንክብካቤ ሳምንት ብሎ በመሰየም በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል፡፡
    በዚህ የምስጋና እና የእውቅና ፕሮግራም በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳድር ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ እንደተናገሩት የጤና ባለሙያዎች እና ክብካቤ ሰራተኞች በኮቪድ ወቅት ህይወታቸውን አሳልፈው በመስጠት ስላገለገሉን በታሪክ ሲዘከረሩ እና በጀግና ክብር በልባችን ይኖራሉ በማለት ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል። ከንቲባው አክለውም አስተዳደሩ ለኮቪድ -19 ወረርሽኝ በጀት ከመመደብ ጀምሮ ሀብት በማሰባሰብና በአጭር ጊዜ የለይቶ ማቆያና ህክምና ተቋማትን በማደራጀት ረገድ ፈጣን ምላሽ መስጠቱን ገልፀው በቀጣይም ወረርሽኙ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ እስከሚደርስ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
    በሌላ በኩልም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የምናስበውን ለውጥ ለማሳካት የሚቻለው ለጤናው ዘርፍ ባለሞያዎችና ሰራተኞች ተገቢውን ክብርና ትኩረት መስጠት ስንችል በመሆኑ ይህ የእውቅናና የምስጋና መርሐ-ግብር መበረታታትና ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት ብለዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝም ሆነ ሌሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለህዝብ በመስጠት እያገለገሉ ላሉ የጤና ባለሞያዎችና ክብካቤ ሰራተኞች በአስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
    የጤና ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው ፈታኝና አስቸጋሪ ጊዜያት ከቢሮው ጎን በመቆም አጋርነታቸውን ላሳዩ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው በተለይም በርካታ ችግሮችን ተቋቁመው በኮቪድ-19 ህክምና መከላከልና መቆጣጠር ላይ የተሰማሩ የጤናው ዘርፍ ባለሞያዎችና ሰራተኞች ውለታ የማይረሳ ታሪክ በመሆኑ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል ብለዋል። በመርሃ ግብሩ በኮቪድ- 19 ምክንያት ህይወታቸው ላለፉ የጤና ባለሞያዎችና ዜጎች የህሊና ፀሎት በማድረግ፣በኮቪድ- 19 በሽታ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች ለባለሞያዎች ምስጋና የማቅረብ፣ለባለሞያዎች የምስጋናና የጭብጨባ እንዲሁም የተለያዩ የጤና ባለሞያዎችን የሚዘክሩ ፕሮግራሞች ተካሂደዋል።
    በምስጋና ፕሮግራሙ ከፍተኛ አስተዋጾ ላበረከቱ ተቋማት እና ማህበራት እውቅና የተሰጠ ሲሆን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ፣ ከነቲባ አህመድ መሀመድ ቡህ ፣ካቢኔ አባላት ፣ የፓርቲ አመራሮች ፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፣ በሞት የተለዩ የጤና ባለሙያዎች ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።