በጉባኤው የከሰአት በኋላ ውሎው ጠዋት የአስተዳደሩ ከንቲባ ባቀረቡት የአስፈጻሚ አካላት የ2013 የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ የአስተዳደር ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና የምክር ቤቱ አባላት አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ በቀረቡ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ’ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የተከበሩ አቶ ከድር ጁሃር እንዲሁም የአስተዳደሩ ከንቲባ ክቡር አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡ በዋነኛነት ትኩረት የሚሹ ተብለው በምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መሃል በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ላይ እየተከሰተ ያለው የዋጋ ንረት ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ምክትል ከንቲባው በሰጡት ምላሽም አላስፈላጊና የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደሩ ክትትልና ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚሁም ማሳያ በሚሆን ሁኔታ በዛሬው እለት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 171 ሱቆች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው በእነዚህ አይነት ነጋዴዎች ላይም የሚደረገው ክትትልና ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይም የአስተዳደሩ ከንቲባ በምክር ቤቱ አባላት በተነሱ የልማት ተነሺዎች የካሳ እና የምትክ ቦታ መሰጠት ጉዳይ’ ህገወጥ የመሬት ወረራ ጉዳይ’ የካፒታል ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል፡፡ በመቀጠልም የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚረጋግጡ ስራዎች ላይ የአስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም የቀረበውን የአስፈጻሚ አካላት የ2013 በጀት አመት ሪፖርት በማጽደቅ የእለቱ ጉባኤ ተጠናቋል፡፡ በቀሪ አጀንዳዎች ላይም በነገው እለት ጉባኤው ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ምንጭ፦የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት


