የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሰራተኞች እና አመራሮች አሸባሪው የህወኅት ቡድን፤ በሰሜን ዕዝ ላይ ባደረሰው ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው፤ በህክምና ላይ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን በመጎብኘት በ20ሺ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ ::
በጉብኝቱ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢስቂያስ ታፈሰ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት ጀግናዉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ለሀገራችን ሉዓላዊነት በሚከፍሉት ከፍተኛ መስዋትነት እኛ በሰላም ወጥተን ሰርተን የምንገባ በመሆኑ ለነዚህ ጀግኖቻችን ያለንን ከፍተኛ አክብሮት እና ድጋፍ ለመግለፅ ይህን ጉብኝት ለማካሄድ በጋራ በመወሰን የመጣን ሲሆን የህን ድጋፍ አጠናክረን የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡
የምስራቅ ዕዝ ሆስፒታል የሀላፊ ተወካይ ኮሮኔል ብርሃኑ ዘዉዱ በበኩላቸዉ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በቅርበት በሁሉም ዘርፍ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በቅርበት እየሰራ ያለዉ ስራ ከፍተኛ መሆኑን አብራተዉ ይህ አክብሮት እና ድጋፍ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን የህግ ማስከበሩን ዘመቻ በፍጥነት እንዲጨርስ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገለፀዋል፡፡ በድሬዳዋ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ የሚገኙት አባላት፤ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡
የቢሮዉ ሰራተኞች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ያላቸዉን ክብር ገለፀዉ እና የህይወትና የአካል መስዋዕትነት እየከፈላችሁ ለምትገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ለሀገር ደጀንነታችሁን የሚያስመሰግን መሆኑንም ገልፀዋል፡፡


