የተከበራችሁ ፦ የአስተዳደራችን ነዋሪዎች
የተከበራችሁ ፦ የእግር ጉዞው ተሳታፊዎች
በቅድሚያ “ኢትዮጵያን ለማዳን የቱንም ርቀት እንጓዛለን፤ የቱንም መስዋዕት እንከፍላለን!” በሚል መሪ መልእክት በተዘጋጀው ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻ የድጋፍ እግር ጉዞ ላይ በመሳተፍና ደም ለመለገስ ፈቅዳችሁ ስለመጣችሁና ለመከላከያ ሰራዊታችን ያላችሁን አጋርነት ስላሳያችሁ በራሴና በድሬዳዋ አስተዳደር ስም ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ።
ሁላችንም እንደምናውቀው አሸባሪው ህውሓት ትላንት በስልጣን መንበር ላይ ተቀምጦ ሲመራት የነበረችውን አገር “ሲኦል ገብቼም ቢሆን አፈርሳታለሁ” ብሎ ያለአንዳች ሀፍረት በአደባባይ አውጇል ።
ይህን ኢትዮጵያን የማፍረስ ቅዠቱን ለማሳካትም ከውጪ ጠላትና ከውስጥ ባንዳ ጋር ተባብሮ ከጦርነት እስከ የኢኮኖሚ አሻጥር ድረስ ዘርፈ ብዙ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።
ይሔ ከስግብግብ የቡድን ፍላጎቱ በስተቀር የአገርና የሕዝብ ሰቆቃና ችግር ደንታ የማይሰጠው አሸባሪ ቡድን የጀመረውን አገር የማፍረስ ከንቱ ቅዠት ለመቀልበስ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያን ለማዳን የትም፣ መቼም፣ በምንም ሁኔታ እዘምታለሁ ብሎ ከግንባር እስከ ደጀን በአንድነት ተሰልፏል።
በአገሩ ላይ ጠላት በተነሳ ቁጥር ቀፎው እንደተነካ ንብ በአንድነት የሚሰለፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀን ከመሆን አልፎ ልጆቹን መርቆ እየላከ ለኢትዮጵያ ክብርና ህልውና መስዋዕትነት ለመክፈል ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
በዚህም አሸባሪው ህውሓት በውጪ ሀይሎች አይዞህ ባይነትና የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ
ታግዞ ጦርነት በከፈተበት ግንባር ሁሉ እራሱ በለኮሰው እሳት እየተለበለበ ሲሆን በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች መስዋዕትነት ረጅም በማይባል ጊዜ የዚህ አገር አፍራሽ አሸባሪ ቡድን ግብአተ መሬት እንደሚፈፀምም ፅኑ እምነት አለኝ።
ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የትም፣ መቼም ፣ በምንም የሚለው ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻው መሪ መልእክት ፡ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በቀጥታ በግንባር በመሰለፍም ሆነ ደጀን በመሆን በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ፣ ባላቸው እውቀትና ችሎታ፤ በየትኛውም ቦታና ጊዜ አገር ለማዳን ዘመቻው የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ የሚያመለክት ነው፡፡
በመሆኑም እኛ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች እስከአሁን ስናደርግ እንደነበረው ሁሉ ለወደፊቱም ለአገር ማዳን ዘመቻው በየትኛውም ጊዜና ቦታ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በደም ልገሳ፣ በሞራልና በመሳሰሉት ድጋፍ በማድረግ የአሸባሪ ቡድኑ ከንቱ ምኞት እንዲከሽፍና አገር የማዳን ዘመቻው እንዲሳካ የውስጥ አንድነታችንን አጠናክረን ልንረባረብ ይገባል ።
በመጨረሻም የጠላት ዋነኛ የጦር መሳሪያ ለሆነው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ጆሮ ባለመስጠት እንዲሁም አንድነትና ህብረታችንን በማጠናከር ፣ የጠላትን የውስጥ ሽኩቻ የመፍጠርና የመከፋፈል
ሙከራን በማክሸፍ ፣ የህዳሴ ግድባችንን በመጨረስና ሌሎች የልማት ስራዎችን በማቀላጠፍ፣ የምናልመውን የኢትዮጵያ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁላችንም በሀላፊነት መንፈስ የዜግነት ድርሻችንን እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያን ለማዳን የቱንም ርቀት እንጓዛለን፤ የቱንም መስዋዕትነት እንከፍላለን!
አመሠግናለሁ !!


