የሀገራችን ሉአላዊነት ላይ ጣልቃ በመግባት አገራችንን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥና የውጪ ጠላቶቻችንን ለመቃወም እንዲሁም ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ” ኢትዮጲያ ታሸንፋለች አንድ ኪሎ ቴምር ለመከላከያ ሰራዊታችን ” በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ አስተዳደር የቅስቀሳ ፣ የቴምርና የሌሎች ቁሳቁሶች የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ሊዘጋጅ ነው ።
በቤዝ-ራም ህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በጋራ በመሆን ሀገር አቀፍ አገርን የማዳን እንዲሁም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራምን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን በተለይም ሰላም በምንም ነገር የማይተካ እንደመሆኑ መጠን ይህንንም ሰላማችንን እያስጠበቁና እያረጋገጡ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ድጋፍ ለማድረግና ከጎኑ ለመቆም ይቻል ዘንድ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ገልፀው በከተማችን ድሬዳዋ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ወጣቱ ትውልድ አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጲያ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የገጠማትን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለማንኛውም ጥሪ መዘጋጀት እንዳለባቸውም ተገልፃል ።
ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በድሬዳዋ ላይ እንደሚካሄድና በዚህ ፕሮግራም ላይ የማርሽ ባንድና የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ የቅስቀሳ ፕሮግራም የሚያካሂዱ ሲሆን ከዚህ ባለፈም የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች ፣ የቲሸርት ሽያጮች እንዲሁም የፊታችን እሁድ የማጠቃለያ ፕሮግራም የሚካሄድ ሲሆን በእለቱም ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፣ ባለሀብቶች ፣ ታዋቂ አርቲስቶችና ግለሰቦች ፣ ባለድርሻ አካላት በፕሮግራሙ ላይ እንደሚገኙ የፕሮግራሙ ኮሚቴዎች ተናግረዋል ።
መላው የከተማችን ነዋሪዎች ፣ ባለሀብቶች ፣ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለዚህ አላማ መሳካት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ተገልፃል።


