አራት መቶ ሺህ ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ እና መድሐኒቶች ለመከላከያ የምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል ድጋፍ ተበረከተ።

    ድጋፉን ያበረከቱት የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና ሂወት ማሞ የመድሃኒት አከፋፋይ ሲሆኑ፣ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ 250 ሺህ ብር የሚገመት መድሐኒቶችና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሁም ሂወት ማሞ የመድሃኒት አከፋፋይ 150 ሺህ ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ በጥቅሉ አራት መቶ ሺህ ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ እና መድሐኒቶች ተበርክቷል።
    በድጋፉ እርክክብ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በአስተዳደሩ ለሆስፒታሉ በአይነት እና በብር የተለያዩ ድጋፎች እየተበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።በቀጣይም ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
    ወ/ሮ ለምለም በዛብህ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊ በበኩላቸው ቢሮው ለሆስፒታሉ ካበረከተው የቁሳቁስና የመድሃኒት ድጋፍ በተጨማሪ 14 የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው ለማገልገል ስራ መጀመራቸውን ገልፀው በቀጣይም ሌሎች ባለሙያዎች በሙያቸው ሆስፒታሉን እንደሚያገለግሉ አመላክተዋል።
    የመከላከያ ምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል ሃላፊ ኮነሬል ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የድሬደዋ አስተዳደር ጨምሮ ነዋሪው እና የተለያዩ ድርጅቶች በተለያየ መልኩ ለሆስፒታሉ ፈጣን እና ተከታታይ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።ይህ ድጋፍ የሃገርን ህልውና ለማስከበር እየታገለ ላለው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሆነ አስረድተዋል።