በሀገራችን ለ34 ተኛ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደግሞ ለ42 ተኛ ጊዜ በመከበር ላይ የሚገኘው የአለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም ለሁለንተናዊ እድገት”በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ መርሀ-ግብሮች በመከበር ላይ ሲሆን ይኸው መርሀ-ግብር ሲጀመርም የድሬዳዋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የጽዳት ዘመቻና የችግኝ ተከላ እንዲሁም የብስክሌት ውድድር ተካሂዷል ።
በዚህም መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ከተማችን ድሬዳዋ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችን ከማፍራቷም በዘለለ የቱሪዝም ማእከል እንደመሆኗ መጠን ከተማዋ ውብና ፅዱ ትሆን ዘንድ ሁሉም ነዋሪዎች የከተማዋን ፅዳት ሊጠበቁ እንደሚገባ ተናግረው የአለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ በሚካሄዱ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በንቃት በመሳተፍ ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኪነ-ጥበብ የስፖርት ብሎም በተለያዩ መስኮች ላይ የነበራትን አስተዋፆና ጉልህ ሚና ማሳየት እንደሚገባም ነው አቶ ከድር ጁሀር በእለቱ የተናገሩት ።


