የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል ለማጠናቅ የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ በ350 ሚሊዮን ብር ውል መግባቱን አስታወቀ ::

    ዩኒቨርሲቲው የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታልን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ የሚያደርግ ውል ከኤ.ቢ ኮንስትራክሽን ጋር በዛሬው ዕለት የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለረጅም ጊዜ በግንባታ መጓተት ምክንየት ሳይጠናቀቅ የቀረውን የድሬደዋ ሪፈራል ሆስፒታል ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ የህክምና ተማሪዎችን የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት ማዕከል እንዲሆን ከድሬዳዋ አስተዳዳር ሙሉ ለሙሉ በባለቤትነት መረከቡ ይታወሳል፡፡
    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታልን ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማዋል ዩኒቨርሲቲው የሶስት መቶ ሀምሳ ሚሊዮን (350 ሚሊዮን) ብር ውል መገባቱን ያስታወቁት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ሪፈራል ሆስፒታሉን ያለበትን የግንባታ ደረጃና ቀሪ ስራዎችን በማስጠናት፣ ለመማር ማስተማር አገልግሎት እንዲውል የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው አሳውቀው በጀት እስኪፈቀድ በነበረው ጊዜ እና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ ስራው ሳይጀመር የተወሰኑ መጓተቶች እንደነበረ ጠቅሰዋል፡፡
    በዛሬው እለትም 70 በመቶ የተጠናቀቀውንና 30 በመቶ ቀሪ ስራዎች የሚቀሩትን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታልን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ከዚህ ቀደም የህንፃ ግንባታውን ሲያከናውን ከቆየው ከኤ.ቢ ኮንስትራክሽን ጋር የውል ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን በዚሁ የውል ስምምነት ወቅትም በአሁኑ ሰዓትም አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀው ቀሪ ስራዎችን በአንድ ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ስራውን አጠናቆ ለመጨረስ የውል ስምምነት ላይ መደረሱን ዶክተር ኡባህ አደም ተናግረዋል፡፡
    የኤ.ቢ ኮንስተራክሽን ስራ አስኪያጅ ተወካይ የሆኑት አቶ ኢዛና አከለው በበኩላቸው የሆስፒታሉን ቀሪ ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለታለመለት አገልግሎት መስጠት እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡