በአሜሪካ ብሎም በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በሚኖሩ የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች አማካኝነት የተመሰረተው የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ማህበር በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚኖሩ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ ከመሆኑም በዘለለ ከዚህ ቀደም ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ መመርመሪያ የሚሆን ማሽን በመግዛት ለአስተዳደሩ ድጋፍ ማድረግ ችሏል ።
የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ማህበር በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚኖሩ አንድ መቶ ለሚሆኑ አነስተኛ ገቢ ላላቸው 100 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ፣ ዩኒፎርም እንዲሁም ለያንዳንዳቸው የ 1000 ብር ድጋፍ ማድረግ ችሏል ።
በድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወሮ ሙሉካ መሀመድ ከምንም በላይ ሀገር የሚገነባው በተማረ የሰው ሀይል እንደመሆኑ መጠን የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ማህበር ባሉበት ቦታ ርቀት ሳይገድባቸው በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ድጋፍ ተማሪዎቹ ለውጤት እስኪበቁ ድረስ በማበረታታትና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ወሮ ሙሉካ በእለቱ ተናግረዋል ።
ላለፍት አራት አመታት ድሬዳዋ ውስጥ ለተለያዩ ወገኖች እገዛ ከማድረጉም በላይ ለክርስትናና እስልምና እምነት ተከታዮች በየበአላታቸው ወቅት እገዛ በማድረግ እንዲሁም ላለፍት ሶስት አመታት ለተማሪዎች የመማሪያ ድጋፎችን ማድረግ መቻሉንም የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ማህበር አባል የሆኑት አቶ አበበ አለማየሁ ተናግረው በያዝነው የትምህርት ዘመን ውጤታማ ለሚሆኑ ተማሪዎች ልዩ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚለገስላቸውም አቶ አበበ ተናግረዋል ።
በእለቱ የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ማህበር የተለያዩ ለትምህርት የሚሆኑ እቃዎችና አልባሳቶችን ድጋፍ የተረከቡት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎች በበኩላቸው ድጋፍ ስለተደረገላቸው ተደስተው በቀጣይም ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል ።


