ኡርጂ ድሬ የዲያስፖራ ማህበር በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ 240 ተማሪዎች የደብተር ድጋፍ አደረጉ ።

    በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች ለትምህርት የሚሆኑ ግብአቶች ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል ። ከዚህ ጋር ተያይዞም በተለያዩ የአለማችን ሀገራት የሚገኙና ኡርጂ ድሬ የዲያስፖራ ማህበር በሚል ስያሜ የተቋቋመው ይሄው ማህበር በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ 240 ለሚሆኑ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች የደብተር ድጋፍ አድርጓል ።
    በዚሁ የድብተር ድጋፍ ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር በተለይም ኡርጂ ድሬ ማህበር በድሬዳዋ ለሚገኙ ተማሪዎች የደብተር ድጋፍ በማድረጋቸው በራሳቸውና በአስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበው በዚሁ ስራ ላይ ለተሳተፍት አመራሮች ፣ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላትም አቶ ከድር ምስጋናቸውን በእለቱ አቅርበዋል ።
    በደብተር ድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙ የተማሪ ወላጆች በተለይም የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተምረው ከራሳቸውም አልፈው ለሀገራቸውም ውጤታማ የሆነ ስራ እንዲሰሩ ነውና ለዚህም ውጤታማነት የተማሪ ወላጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ\ሮ ሙሉካ መሀመድ ተናግረዋል ።
    ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ ለትምህርትና ለተማሪ የሚደረግ ድጋፍ እንደሆነና ትውልድን ብሎም ዜጋን ከጨለማ ስፍራ አውጥቶ ወደ ብርሀን አሻግሮ ነገ ላይ ሀገርን የሚተካና የሚረከብ ትውልድ እንዲፈራ ካስፈለገ ለተማሪዎች ድጋፍ ማድረግ ነውና ይህንን ድጋፍ ላደረጉ አካላት የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
    ትምህርት ለሁሉም በጣም አስፈላጊ ሲሆን ይህንንም በማሰብ የደብተር ድጋፍን ያደረጉት አካላት በአብዛኛው በጅዳና በተለያዩ የአለም ሀገራት የሚገኙ ሲሆኑ ኡርጂ ድሬ የሚል ማህበር በመመስረትና አንድነትን በመፍጠር ድሬዳዋ ላይ ድጋፍ በማድረግ ማህበሩ የሰራቸውን ስራዎች ሌሎችም እንደምሳሌ በመውሰድ እንዲሰሩ በማለም ድጋፍን ማድረጋቸውንም ነው የድጋፍ አስተባባሪ የሆኑት ወ\ሪ ሳርቱ ሸምሹዲን የተናገሩት ።
    በተለይም የድሬዳዋ አስተዳደር ዳያስፖራ ማስተባበሪያ በተለያዩ የውጪ ሀገራት የሚኖሩ የከተማዋን ተወላጆች በማስተባበር ባለፍት ሶስት አመት አረጋዊያንን በመደገፍ ፣ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችንና ወላጅ አልባ ለሆኑ ህፃናት ድጋፍ መደረጉን የድሬዳዋ አስተዳደር ዲያስፖራ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አክሊለ ታጠቅ ተናግረው በቀጣይም ድሬዳዋ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላቶች ጋር በመነጋገር የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው አቶ አክሊለ በድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይ የተናገሩት ።