የዴንጊ ትኩሳት በሽታ ወረርሽኝ በአስተዳደራችን መከሰቱና የጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

    የደንጊ ትኩሳት በሽታ ወረርሽኝ በየዓመቱ ዝናብን ተከትሎ እንደሚከሰት የሚታወቅ መሆኑንና በዚህ ዓመትም 87 ናሙና ወደ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተልኮ 4 ሰዎች በደንጊ ትኩሳት በሽታ መያዛቸውን የሚያረጋግጥ የምርመራ ውጤት መገኘቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ለሚዲያ ባለሞያዎች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
    ኃላፊዋ አያይዘውም የዴንጊ ትኩሳት በሽታ በፍጥነት የሚተላለፍና እስከሞት የሚያደርስ በመሆኑ ህብረተሰቡና ፅዳትና ውበት ኤጀንሲን የመሳሰሉ መስሪያቤቶች በጋራ አካባቢን የማፅዳትና ቢንቢን የማጥፋት ሥራ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው እና ወረርሽኙ ተስፋፍቶ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን የመከላከሉን ሥራ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
    በዚህ ዓመት አጎበር ለሁሉም ቤተሰብ በከተማና ገጠር የተዳረሰ በመሆኑ አጎበሩን በትክክል ለተሰጠበት ዓላማ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
    ወ/ሮ ለምለም ጨምረውም በየዕለቱ በማህበራዊ ሚዲያዎቻችን እንደምናሳውቀው በኮቪድ – 19 ምክኒያት በአስተዳደራችን የሞት ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ሰዓት ድረስ የ 100 ሰዎች ህይወት ማለፉን በጠና የሚታመሙ እንዲሁም የሞት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መሆኑንና በተለይ ዴልታ ቫርያንት ብዙ ሰዎችን እያሳጣን በመሆኑና የህክምና ባለሞያዎቻችንንም ዋጋ እያስከፈለ ከመሆኑም ባሻገር ህብረተሰቡም የህክምናውን ውድነት መቋቋም ስለማይችል ከ 3 – 10 ብር ማስክ በመግዛት እራሱንና ሌሎችንም ከኮቪድ መጠበቅ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
    በተለይ ከቀን ወደ ቀን የኮቪድ ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ ቤታቸው እንዲቀመጡ ያደረግናቸው ታማሚዎች በቸለተኝነት ከህብረተሰቡ ጋር እየተቀላቀሉና ትክክለኛ አድራሻቸውንም ያለመናገር ሁኔታዎች በመኖራቸው የኮቪድን ስርጭት እያስፋፋው ሲሆን ህብረተሰቡና ተቋማት የወረርሽኝኑን መስፋፋትና የበሽታውን ከባድነት ግምት ውስጥ አስገብተው የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባቸው አበክረው አሳስበዋል የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ፡፡
    ምንጭ ፡- የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ