በስነ -ስርአቱ ላይ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እንደተናገሩት የኢትዮጰያ ጠቅላይ ሚኒስተር ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ስራውን የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ተቀብሎ በአስተዳደሩ ላደረጉት በጎ ተግባር በአስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን በማቅረብ በቀጣይ ከለመድነው የስራ ባህል በመውጣት በአዲሱ መንግስት አዲስ ምዕራፍ ተከትለን ለህብረተሰቡ የገባነውን ቃል ለመተግበር ቀንና ለሊት እንሰራለን ብለዋል።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስተርና የድሬዳዋ አስተዳደር በጋራ በመሆን የአቅመ ደካሞች ቤቶችን የመገንባት የበጎ ስራ በቀበሌ 03፣04፣08፣09፣02፣01 አስር ቤቶች ገንብተው ለተገነባላቸው ግለሰቦች አስተላልፈዋል።
በስነ-ስርአቱ ላይ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የመጡ አመራሮች ጋር በመሆን የቤት እርክክብ ስነ-ስርአት ተካሄዷል ።
የተገነባውን ቤት የተረከቡ አቅመ ደካሞችም ስለተደረገላቸው አመስግነዋል። ለሰው ልጅ መሰረታዊ የሆነው የቤት ችግር ውስጥ ሆነን ልጆቻችንን እያስተማርን ባለንበት ሁኔታ ይህን ችግራችን ለመቅረፍ ከወደቅንበት ተመልክታችሁ በላያችን ላይ የፈረሰውን ቤት እንዲህ ባማረ ቤት ገንብታችሁ በማስረከባችሁ እናመሰግናለን በማለት።
በቀጣይም የእለት ጉርስ የሚያገኙበት የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ለአስተዳደሩ ከንቲባ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቤቱ ለተገነባላቸው አቅመ ደካሞች በአስተዳደሩ የማህበረሰብ ተሳትፎ ልማት ኤጀንሲ አስተባባሪነት ባለሀብቶችን፣ኮንትራክተሮችንና ግለሰቦችን በማስተባበር የአልባሳት፣የቤት ቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
በስነ-ስርአቱ ማጠቃለያ በበጎ ስራው ለተሳተፉ ተቋማት እና ለተቋራጮች የምስጋና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።


