በከተማችን ድሬዳዋ ላይ የተለያዩ በኤክስፖርት ስራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶና ተቋማት ፣ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማቶች ፣ እንዲሁም ከ 15 በላይ የሆኑ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል ።
በዚህም ውይይት ላይ በተለይም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውና የውጪ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ ተቋማት ላይ ያሉትን ችግሮች በመነጋገር በቀጣይ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ፎረም ለመመስረት ታልሞ ውይይቱ መካሄዱን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጅሀር ተናግረው እንደዚህ አይነት መሰል ውይይት በየወሩ ለማካሄድ ከመታቀዱም በዘለለ የጋራ እቅድና የጋራ ስምምነት ኖሮ ከተማዋን ለማሳደግ በትኩረት መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ውይይት መደረጉን አቶ ከድር ተናግረዋል ።
አቶ ከድር ጁሀር አክለውም ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩና የውጪ ምንዛሬ የሚያመጡ ኢንቨስተሮች የሚያጋጥማቸው ችግሮች በውውይቱ ላይ እንደተነሳና ከዚህ ባለፈም ከኮንትሮባንድ ጋር ተያይዞ በቀጣይ በምክትል ከንቲባ እየተመራ ላሉት ችግሮች መፍትሄ እየተሰጠበት የሚኬድ መሆኑንም ነው አቶ ከድር ጂሀር የተናገሩት ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በውይይቱ ላይ በተለይም የትራንስፖርት ማነስ ፣ የኬላዎች ቁጥር መብዛት ፣ በኤክስፖርት ምርቶች ላይ እሴት አለመጨመርና ሌሎች ችግሮች በውጭ ንግዱ እድገት ላይ ተፅእኖ እንዳሳደሩ የተቋማቱ አመራሮችና አባላት በውይይቱ ላይ አንስተዋል ። በቀጣይም ለዘርፉ እድገት አስተዳደሩ ከተቋማቱ ጋር በሰነድ የተደገፈ ቀልጣፋ እና ችግር ፈቺ የሆነ የግንኙነት አግባብ ለመፍጠርም ከስምምነት ላይ ተደርሷል ።


