የድሬዳዋ አስተዳደር ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን የ 2014 በጀት አመት የደንበኞች ፎረም መድረክ ያካሄደ ሲሆን በመድረኩ ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር በቀደሙት ጊዜያት የባለስልጣኑ የቦርድ ሰብሳቢ ሳሉ የጀመሩትን ጥረት አጠናክሮ በማስቀጠል በተቋሙ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚደግፍም አቶ ከድር ገልፀው በተለይም በደንበኞች ፎረም የሚነሱ ሀሳቦች ገንቢ ስለሆኑ ህብረተሰቡ በግልፅነት ጥቆማዎችንና የአሰራር ግድፈቶችን እንዲታረሙ ሀሳብ እንዲሰጥም ጠይቀዋል ።
አቶ ከድር ጁሀር አክለውም አስተዳደሩ በአዲስ መልክ ለጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ መላው የአስተዳደሩ ነዋሪ ድጋፍን እንዲሰጥም ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።
ከዚህ ቀደም የባለስልጣኑ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ከድር ጁሀር ሀላፊነታቸውን ለአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ ለሆኑት አቶ ሀርቢ ቡህ ያስረከቡ ሲሆን በዚህ ወቅትም ንግግር ያደረጉት አቶ ሀርቢ ቡህ የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣትም ቃል ገብተዋል ።
የደንበኞች ፎረም ለተቋሙ ለውጥ ሰፊ ውጤት ያስገኘ መሆኑንም የድሬዳዋ አስተዳደር ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መሀመድ ሙሴ በእለቱ አንስተው በቀጣይም ህብረተሰቡ ከተቋሙ ጋር አብሮ የመስራት ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል ።


