አሸባሪው የህወሃት ቡድን ጥቅምት 24 \ 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ የሚዘክሩ የተለያዩ መርሃ-ግብሮች በድሬዳዋ አስተዳደር ተካሂደዋል ። በመርሀ ግብሮቹ ላይም ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚያስታውሱና የሚዘክሩ ስራዎች ከመቅረባቸውም ባለፈ የጧፍ ማብራት ስነ-ስርአትም ተካሂዷል ።
በዚሁም መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ለአገርም ሆነ ለህዝብ ግድ የሌለውና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ያለን የጥፋት ቡድን እስከወዲያኛው ለመደምሰስና አገርንና ህዝብን ከጥፋት ለመታደግ ዳግም ቃል በመግባት ህይወቱን ለእናት አገሩ ያለስስት እየሰጠ ካለው ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ጎን በአንድነትና በቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚገባ አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው በተለይም የሀገራችን ኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ በሆነው የሰራዊታችን ሰሜን እዝ ላይ የደረሰው ነውረኛ ጥቃት በእያንዳንዳችን ላይ እንደደረሰ የሚቆጠር ጥቃት በመሆኑ የተፈፀመውን ግፍ እያወገዝኩ ሠራዊቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈፀም በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ያላንዳች ማወላወል ከሰራዊቱ ጎን የሚሰለፍ መሆኑን አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
በተለይም ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ ከተማዋን የሰላምና የፍቅር ከተማ ትሆን ዘንድ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ በሀገር መከላከያ ሚኒስትር የሀረሪ ክልል የድሬዳዋ አስተዳደር ላይዘን ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት ኮረኔል ዮናስ ሮቤል ተናግረዋል ።
በመርሀ-ግብሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው ሀገራችንን ከጥፋት ሀይሎች ለማዳን ግንባር ድረስ እንደሚዘምቱ ተናግረው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የመንግስት ሰራተኞችን አሳታፊ ያደረገ ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይቶቹ ላይም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል ። በድሬዳዋ አስተዳደር ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት በተዘጋጁት መርሃ ግብሮች ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ፣ የመንግስት ሰራተኞች ፣ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የፀጥታ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።


