የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማትና የማህበረሰብ መሪዎች
አገር አፍራሽ አሸባሪ ቡድኖች ለመገርሰስ የማካሄደው ዘመቻ በስኬት እንዲደመደም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የኃይማኖት ተቋማት መሪዎች ፣አባገዳዎችና ዑጋዞች ተናገሩ፤
የኃይማኖት ተቋማት መሪዎቸና አባገዳዎችአገርና ሠላም የሌለው ሰው ምንም ስለሌለው አገርን መጠበቅ ቀዳሚ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የኃይማኖት ተቋማትና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ኡጋዞችና አባገዳዎች በአገር ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ውይይት አድርገዋል ።
በውይይቱ የተሳተፉ የኃይማኖት አባቶች እንደተናገሩት ፤ አገርን ለማዳን ከፀሎትና ከምህላ በዘለል አሸባሪዎችን ለመገርሰስ የሚደረገውን ዘመቻ እንዲሳካ ግንባር ድረስ ተጉዘው ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ።
አባ ኢሳያስ ገብረስላሴ ጁንታው የወያኔ ወራሪ ኃይል ቤተ እምነቶችንና መስጂዶችን በማፈራረስና ንፁሃንን በመጨፍጨፍ አረመኔያዊና ሰይጣናዊ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
“ይህን አገር አፍራሽ ቡድን መዋጋት በራሱ ፅድቅ ነው፣ሰማዕትነት ነው፣ ካስፈለገ ግንባር ተጉዘን አገርን ማዳን ተግባር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን”
ወንድም ሚልኪያስ ታዬ በበኩላቸው በመላው አገሪቱ የሰይጣን ተግባራትን የሚከውኑ ሽብርተኛ ሐይላት እንዲጠፉ ሁሉም በፆምና በፀሎት እየተጋ መሆኑን ተናግረዋል ።
ከዚህ በተጨማሪ አገርን ለማዳን እየተካሄደ የሚገኘው ዘመቻ እንዲሳካ በየአብያተ ክርስቲያን የገንዘብ ፣የቁስና የምግብ ድጋፍ ኦየተሰበሰበ መሆኑም ገልፀዋል ።
ዘመቻው የሞት ሽረት በመሆኑ እስከመጨረሻው ድረስ ወጣቶችን ወደ ግንባር እንዲጓዙ በማድረግ፣ለተፈናቀሉት ወገኖች አስፈላጊውን ድገፍ በማድረግ እና ሠራዊቱን ባለን ሁሉ ከጎኑ በመቆም የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነዉ ያሉት ደግሞ የአፍረንቀሎ አባገዳ አቶ አብዱራዛቅ አህመድ ናቸው።
እሳቸው እንደተናገሩት ፤ሁሉም የሚሆነው አገር ሲኖር በመሆኑ አገርን ከሽብርተኞቹ ህወሃት ና ከህወሓት ያልሰመረ ጋብቻ ከፈፀመው ኦነግ ሸኔ ማዳን የመከላከያ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።
ይህን ተልዕኮ ለማሳካት በምስራቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቁስ፣የገንዘብ ና የሰው ኃይል ማሰባሰብ መጀመራቸውን ተናግረዋል ።
ሊቀ -ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው በበኩላቸው በሁሉም በቤተክርስቲያናት አገር ለማዳን ዘመቻው መሳካትና ለተፈናቀሉ ድጋፍ የማድረግ የተቀናጀ ዘመቻ ተጀምሮ እየተገባደደ ይገኛል ብለዋል።
አገርን ማዳን ከአካባቢ ስለሚጀምር በአንድ መንፈስና ልብ የወያኔን አገር አፍራሽ ተላላኪዎች ማፅዳት እንደሚገባ አሳስበዋል ።
በተለይ ሰይጣዊ ድርጊት እየፈፀመ የማገኘውን ህውሃት ማጥፋት ፅድቅ እንጂ ኃጥያት ባለመሆኑ አገሪቱን ለትውልድ ለማቆየት አሸባሪዎች ና የውጭ አገር አፍራሽ ሴራ ጠንሳሾችን በተባበረ መንገድ ማጥፋት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
ሼህ ኤሊያስ አልይ እምነታችን መስጂዶች ተከብረው እንዲኖሩ ዜጎች እንደ ሶሪያና የመን አገር አልባ ሆነው ለስደት እንዳይዳረጉ አገርን ከሽብርተኛው ወያኔ ወራሪ አጥፊ ቡድን ማዳን የህልውና ጉዳይ አድርገን እየተጋን እንገኛለን ብለዋል።
አቅም ያለው በአቅሙ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ አገርን ለማዳን እየተሰለፈ ይገኛል፤ ይህ እስከመጨረሻው ድል ድረስ ይቀጥላል ብለዋል።
ህዝቡ ለማይቀረው የመጨረሻው አገር የማዳን ተግባር ለጀአድ የህልውና ጦርነት መነሳቱን ጠቁመዋል።
“ከዛሬ ጀምሮ ምሳሌ ለመሆን ከለኝ ሃብትና አልባሳት ግማሹን አገር ለማዳንና በጦርነት ለተፈናቀሉት ለመስጠት ወስኛለሁ” ብለዋል።
ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች አገርን ለማዳን ሁሉም በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሰ የሚፈለገው ውጤት በፍጥነት ዳር እንደሚደረስ ገልጸዋል ።
በውይይቱ የተወሰደው አቋምና እየተሰበሰበ የሚገኘው ድጋፍ የአገር ለማዳን ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረው በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተናግረዋል ።
ምንጭ:- ኢዜአ


