ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የስራ እድል ፈጠራ አይነተኛ አስተዋፆ እንደሚመጣ የሚታመን ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞም በድሬዳዋ አስተዳደር ከተካሄደው አዲስ የመንግስት ምስረታ ጋር ተያይዞ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራባቸው ካሉ ስራዎች አንዱ የስራ እድል ፈጠራ ነው ። በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ ወጣቶች ጊዜያዊም ሆነ ቋሚ የሆነ የስራ እድልን በማመቻቸት ወደ ስራ ይገቡ ዘንድ የድሬዳዋ አስተዳደር ቴክኒክ ሞያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ።
ከነዚህም ስራዎች አንዱ ከተለያዩ የሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጤና የትምህርት መስኮች ተመርቀው ነገር ግን የስራ እድልን ላላገኙ የከተማዋ ወጣቶች ከዶት ግላስ ኢትዮጲያ ጋር በጋራ በመሆን በአይን በአይን ምርመራና የመነፅር ስራ ላይ ይሰማሩ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የስራ እድል መፈጠር ተችሏል ።
በተለይም ወጣቶቹ የሚሰጡት የመነፅር ስራ አገልግሎት በሌሎች አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ የሚያስወጣውን ስራ እጅግ በጣም አነስተኛ በሆነ ዋጋ አገልግሎት ከመስጠታቸውም በዘለለ የአይን መነፅር ተጠቃሚ የሆኑ አካላት ወጣቶቹ አገልግሎት በሚሰጡበት ቦታ ሄደው አይናቸውን ተመርምረው ያለምንም የጊዜና ቀን ቀጠሮ ወዲያውኑ በተመረመሩበት ሰአት ለአይናቸው ተስማሚ የሆነ መነፅር እንደሚሰጣቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ቴክኒክ ሞያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግሯል ።
አቶ ሮቤል አክለውም እነዚህ ወጣቶች ወደ አይን ምርመራውና የመነፅር ስራው ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊውን ስልጠና እንደወሰዱና በመጀመሪያው ዙርም ለ 20 ወጣቶች የስራ እድሉ እንደተመቻቸላቸው አቶ ሮቤል ተናግረው ለእያንዳንዳቸውም 60 መነፅር እንደተሰጣቸውና በዋጋም ሲተመን አንዱ መነፅር 300 ብር ሲሆን ለአንዱ ወጣትም 18 ሺህ ብር የሚያወጣ መነፅር በነፃ ተሰቷቸው ወደ ስራ እንደገቡና በቀጣይም ደግሞ አስፈላጊውን ሁሉ ስልጠና እየተሰጣቸው ሌሎች ወጣቶች ወደ ስራ እንደሚገቡም ነው አቶ ሮቤል የተናገሩት ።
የስራ እድል ምችችት የተደረገላቸው ወጣቶች በበኩላቸው በጤና የትምህርት መስክ ተመርቀው ነገር ግን ለበርካታ ጊዜያት ምንም አይነት ስራ እንዳልነበራቸው ተናግረው አሁን ላይ ግን በተመቻቸላቸው የስራ ፈጣራ በእጅጉ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በዚሁ የአይን ምርመራና የመነፅር ስራ ተጠቃሚ የሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች በበኩላቸው ወጣቶቹ በሚሰጡት አገልግሎት ደስተኛ ከመሆናቸውም ባለፈ ለወጣቶቹ በተፈጠረውም የስራ እድል እንደተደሰቱና መንግስትም ለወጣቶቹ ላደረገላቸው የስራ ፈጠራም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።


